top of page

    ግጥምና የሀዘን እንጉርጉሮ

ለወይዘሮ  አልሚዝ  ኃይሌ የተገጠሙ ግጥሞችና
 የሀዘን እንጉርጉሮ

 

የእማዬ ትዝታ

ከወርቅአበባ ሻውል

 

ልትሰናበችን ጉዞሽን ጨርሰሽ

ጤናሽም ታወከ እማምዬ ደከምሽ

እግርሽም ደከመ መሄድም አቃጠሽ

ከዘራ ቀረና በዎከር ሆነ እርምጃሽ

ክዛም ቀጠለና ዊል ቸር አስፈለገሽ።

 

ፍቅርሽ አየለና ድንግል ማርያም ቤት

ቤት አገኘችልሽ ሆንሻት ጎረቤት።

ደስታሽ ወሰን አጣ በጣምም ደስ አለሽ

እቤት እስክትቀሪ ሕመሙ ጠንቶብሽ።

በሽታው ከልክሎሽ መብላት መጠጣት

ስውነትሽ ክሳ አጣሽ አቅም ጉልበት።

ከአልጋ መውጣት መውረድ ፍጱም አስቸገረሽ

ለመገላበጡም ሁለት ሰው አሰፈለገሽ።

እማዬ ምን በላች ሆነ ሰላምታችን

ጠላት ስታደርጊው ብዪ የሚልሽን።

 

ስለሺ ወንድሜ ይህን ትዕይንት አይቶ

የጥንቷ እማምዬ ተረሳችው ከቶ።

በአይነ ልቦናው የምትመጣበት

ይችው ምስኪን ሆነች አዲሲቷ እናት።

 

ወንድሜ ላስታውስህ የእማዬን ትዝታ

በልብህ አኑረው የፍቅሯን ፈገግታ።

አንዴት ይረሳሃል ሆነን ሕጻናት

የጥንቷን እማዬን ጠንካራዋን እናት።

ማለዳ ቀስቅሳን እኔንና አንተን

በስነ ስርዓት ነጠላ ለብሰን

እጃችንን ይዛ መኪና እንዳይገጨን

እንጏዝ ነበረ ልደታ ቤተስኪያን።

አቤት እርምጃዋ እንዴት ፈጣን ነበር

የእኛ ሁለት እርምጃ ለእርስዋ አንድ ነበር።

 

"ከኤል ኤ ሪቨር ሳይድ ልጠይቅ መጥቼ

ቤተሰቤን ትቼ ስራዬን ሰውቼ።

እማምዬ ናፍቃኝ ብመጣ ላወጋት

ጊዜው ተቃጠለ እንቅልፉ አሸነፋት።

የተጨዋወትነው ጊዜውን ባስበው

አይሞላም ደቂቃ እንቅልፏ ወሰደው።"

ብለህ ስትናገር ስለሺ ሰማሁህ

ወንድሜ አውጣው ይህንን ከአዕምሮህ።

 

ላስታውስህ ወንድሜ የጥንቱን ትዝታ

ማለዳ የምትነቃ በልዩ ደስታ

እናትህ ነበረች አምራ በፈገግታ።

አይናችንን ሳንገልጥ እኛ ሳንነሳ

ፀጉሯን አበጥራ ቆንጆ ጥበብ ለብሳ

ጥግ ትቆም ነበር መቁጠሪያዋን ይዛ።

 

ቹቹዬ አትዘኚ በአዲሲቷ እናትሽ

አይን አይንሽን ስታይ ልትጠይቂያት መጥተሽ

ጠብቀሽ ነበረ ሚስጥር እንድትነግርሽ

አይነ አፋር ልጅ ሆነች ትጫዋችዋ እናትሽ

ልሳን አንደበቷ ፍፁም ቀዘቀዘብሽ።

እርሺው የእናቴ ልጅ መሪሩን ትዝታ

አዕምሮሽ ውስጥ ይሳል የእናትሽ ፈገግታ።

ቹችዬ ላስታውስሽ የአልማዝዬን ነገር

የምታጫውትሽ ሚስጥር ከቁብነገር።

አስታራቂ ይጠፋል ብላ ተጨንቃለች

አስታርቂልኝ ብላ ሹመት ሰጥታሻለች።

 

ከሁሉ አሳዘንሽኝ ሚሚዬ ምን ላርግሽ

እማምዬ ጠፋች እናት አስከባሪሽ።

ለአዲሲቷ እናት ብዙ ደከምሽላት

ሞትን ልትመልሽው አልቻልሽም የኔ እህት።

ብዙ ጊዜ ክሞት አፋፍ የዳንሽው

በጥንቷ እማምዬ በፀሎትዋ ነው።

ሚሚዬ ይከተልሽ የጥንቱ ትዝታ

ምክርዋን ተቀበዪ አለብሽ ውለታ።

 

ተጫዋቹ ወንድሜ መስፍኔ አትዘን

ልታስቅ ሞክረህ ምስኪኗ እናትህን

አልቻለችም ክቶ ልትረሳ ህመምዋን።

አዲሱን ትዝታ በድሮው ለውጠው

መንፈስ የሚያድስው ሳቅዋን አስታውሰው።

እማ ሙሉ ሽሮ ብለህ ስትናገር

ትስቅልህ ነበር ግንባርዋም ቢቋጠር።

እስቲ ልመልስህ ወደ ኋላው ዘመን

የእማምዬ ጸሎት አንተን ለማዳን

በችግሩ ጊዜ በዛ በቀውጢ ቀን።

ችግር ተካፋይዋም አንተ ብቻ ነበርክ

ዋርካ ምግብ ቤትን አብረሃት መሰረትክ።

 

 

ቢጡዬ የኔ እህት ሀዘን ባንቺ ባሰ

ጥላ ከለላችን በአፈር ተለወሰ።

ምስኪንዋን እማዬ በጣም አስታመምሻት

አልባሽዋም ሃኪምዋም ወጥቤቷም ሆንሽላት

እናትሽ ሄዳለች ውለታሽ በዝቶባት

ደከመኝ ሳትይ ስላስታመምሻት።

ይልቅስ ልንገርሽ የጥንቱን ትዝታ

ያንቺና የእማዬን የፍቅር ትውስታ።

ገና ልጅ እያለሽ የአራት አመት

እናታችን ገባች የማታ ትምህርት።

የእናታቸን ፍቅር አላስችል ብሎሽ

ትከተያት ነበር ደብተርሽን ይዘሽ

እያንቀላፋሽም ብዙ ስላስቸገርሽ

ቤተሰቡ ሁሉ በተለይ አባትሽ

እቤት እንድትቀሪ በጣም አስገደዱሽ።

አንቺ ግን ብልጥ ነሽ ብትሆኚም ህፃን

አልሻቸው አሞኛል ሆዴን እራሴን።

አልድንምም ስላልሽ እናቴን ካላየው

እማዬም ሰለቻት ትምህርቱን ተወችው።

 

ዶክተሩ ወንድሜ አንዳርጋቸው ሻውል

እንዴት ሳላድናት ቀረሁ አትበል።

ሀዘንህ ረበሸኝ ፀፀትህን ሰማሁ

ወንድሜ ተጽናና ፈቃዱ ከአምላክ ነው።

ነገር ግን ቅረፀው በአይነ ልቦናህ

የእማዬን ትዝታ አለኝታ ፍቅርህ

ሁሌ የሚገረመኝን ልመስክርልህ

እንደአባትዋ ነበርክ እሷ አንደልጅህ።

ቃልህን ጠባቂ አጣህ አክባሪህን

ትኮራብህ ነበር ውዷ እናታችን።

 

ገበያነሽ እህቴ እድለኛ ነሽ

አዲስዋን አማዬ ሳታዪ ባይንሽ

ክስታ ጠቋቁራ ያች ቆንጆ እናትሽ

ወደ ሞት ስትጟዝ ሳታያት አመለጥሽ።

ተንክባከቢልኝ ነችና አበባዬ

የኔ እማምዬ ያንቺ አልማዝዬ።

 

ትንሹ ኤልያስ ስማኝ ልንገርህ

ብዙ ነው የማውቀው ስለልጅነትህ

በጣም ታመህ ነበር በህፃንነትህ።

በልቤ ተቀርጿል የእማዬ አበሳ

አንተን ስታስታምም ሌሊት ስትነሳ።

ሞግዚት ሰራተኛን ሁሉን ሳታምን ቀርታ

አማዬ አዳነችህ በፈጣሪ እርዳታ።

 

የዚህ ግጥም መልዕክት ገብቷችው ይሆናል

የእማዬ ትዝታ በሁለት ይከፈላል።

አንደኛው ይባላል አዲሱ ትዝታ

ይለናል አትርሱ የእማዬን በሽታ

ሁለተኛው ደግሞ የጥንቱ ትዝታ

ልዩ ስሜት አለው ብሩህ የፈገግታ።

 

የጥንቱን ትዝታ እማዬ መርጣለች

ጥንት እንደነበርኩት አስታውሱኝ ብላለች።

ትታያችው እማዬ በፍቅር ፈገግታ

ቤተክርስትያን ውስጥ ስትዘምር በእልልታ።

ጤናዋን ጠባቂ ስፖርት የምትሰራ

የስው መውደድ ያላት መንፈሰ ጠንካራ።

ሰውን ሰላም ስትል ጊዜ የሚፈጅባት

ጌታዬ እመቤቴ የምትለው ትሁት።

ችግረኛ ለጋሽ ዘመድ ሰብሳቢዋ

የኛ አስታራቂ ቆንጆ ሽቅርቅርዋ።

ስንወልድ ስታርስን ነበረች ክርታታ

የምናስታውሰው ይኸው ነው ትዝታ።

 

መሞትዋን ሰምታችሁ የደነገጣችሁ

በርስዋ ፍቅር መዳፍ የተዳሰሳችሁ።

መሆንዋን አወቅን የብዙሃን እናት

በፍቅሯ ተነክቷል የብዙ ስው ሕይወት።

ሞትስ ብርቅ አይደለም ስው ሁሉ ይሞታል

ፍቅር ግን ታላቅ ነው ዘላለም ይኖራል።

አደራ ትላለች  እማዬ የኛ እናት

ለወገን ለትውልድ ፍቅሬን አስተላልፉት።

 

ዘመድ ወዳጆችዋ አትቀየሙን

እምቢ ስንላችሁ እንጠይቅ ስትሉን

አሁን ግን ይግባችሁ አደራ አለብን

እማምዬ አትወድም ታሞ መታየትን።

እነ ኣባ ታማ ሊጠይቋት መጥተው

ቆማ ተራመደች ወጥታ ሸኘቻቸው።

 

ስለዚህ እማዬ አደራ ትላለች

ጥንት እንደነበርኩት ኣስታውሱኝ ብላለች።

                              -----------------------------------------------------------------

 

 

 

አቤል አድማሱ

ቶሮንቶ ካናዳ

 

“ሞትም አለ ለካ”

 

እጅ እነሣለሁኝ እኔስ ለልማዴ

ጉልበትዎን ልሳም እኔስ ለልማዴ

እርስዎም ይመርቁኝ እንዲጠና ክንዴ

ወደሞት አይሂዱ አንዲቷ ዘመዴ

አንጄቴ አልችል አለ ተለወሰ ሆዴ።

 

ያሰብነው ቀረና ግዜን ግዜ ተካ

በዘመን ፍጻሜው ሞትም አለ ለካ።

እማምዬ የሁሉ እናት

 

አይበገሩዋ የሴት ወንዷ እናቴ

እርስዎን እንዴት ልርሳ ሳይደርስ ቀን ሞቴ።

የሴቶቹ ቁንጮ ታላቅ ሴት ወይዘሮ

ታሰረ አሉኝ እጅዎ ምን ነካው ዘንድሮ

ለሰው ሁሉ አዛኝ ለኔ ተጨናቂ

የሚስጢር ግምጃ ቤት ባልትናን አዋቂ።

 

ያሰብነው ቀረና ግዜን ተካ

በዘመን ፍጻሜው ሞትም አለ ለካ።

እማምዬ የሁሉ እናት

 

ለዚህ ሁሉ አመታት አብረን ስንኖር

መካሪ ተቆጪ የወንጌል መምህር

በትዕግስት መቻሉን ያስጠኑኝ ነበር።

ላልቅስልሁ እንጅ እምባዬን ላፍሰው

እስከመጨረሻ ለማይገኙት ሰው።

ክብርት አልማዝ ሀይሌ እውነተኛ ሴት

የርስዎን ሀቀኝነት የርስዎን ሀይማኖት

በቂ ቃል አጣሁኝ የምገልጽበት።

 

ያሰብነው ቀረና ግዜን ግዜ ተካ

በዘመን ፍጻሜ ሞተም አለ ለካ

እማምዬ የሁሉ እናት

 

መወለድ ቋንቋ ነው ፍቅር ቁም ነገር

አስተሳስሮን ነበር ጌታ እግዚአብሄር

ምነዋ በሆነ እንደርስዎ ሰው ሁሉ

ተቀብሎ የሚሸኝ ሁሉን እንዳመሉ።

ከወደዱ አይጠሉ ካቀረቡ አይርቁ

መስጠት መርዳት እንጅ ወረትን አያውቁ

አወይ አልማዝ ሀይሌ ቀን አለማወቁ።

 

ያሰብነው ቀረና ግዜን ግዜ ተካ

በዘመን ፍጻሜ ሞተም አለ ለካ

እማምዬ የሁሉ እናት

 

እንደው በደፈናው አባቶች እንዳሉት

ታቦታችን አልማዝ የሁላችን እናት

እንደእናት አሳቢ እንደአባት መካሪ

እንደወንድም ጋሸ እንደተቆርቋሪ

እንደቅርብ ጓደኛ እንደቅርብ ወዳጅ

ለክፉም ለደጉም ምክርዎ የሚበጅ

ለኔ አማካሪዬ አሳቢ ህይወቴ

የእናቴ ምትኳ የእህቴና አባቴ

ሲጨንቀኝ ሲከፋኝ ፊቴን ተመልክተው

ችግሬን አቃላይ ምክርዎ መድሀኒት ነው

ያሰብነው ቀረና ግዜን ግዜ ተካ

በዘመን ፍጻሜ ሞተም አለ ለካ

ተነጋግረን ነበር ታላቅ ቁምነገር

ቤተሰቤን ይዤ አብረን ልንኖር

ያልተሳካ ጉዞ እኛ ብዙ አላሚ

ለካ ሞትም አለ እንዲህ አስቀያሚ።

 

እማምዬ የሁሉ እናት

 

እማምዬ የኛ እናት እንዲህ እንደዋዛ

የመልካም ዘር ሀረግ የልጆችሁ ቤዛ

የሻውል ቅምጥል አጋር ለትዳር

የበጅሮንድ ሀይሌ የጎልማሜ ዘር

የሴቶች ቁንጮዋ የወርቅ አበባ ዘር

የማሚቴ ሀይሌ የዚያች ቆንጆ ዘር

የቤቱ ምሰሶ ዋልታና ማገር

ቤቱስ ትልቅ ነበር ቀረ በሀገር።

 

ያሰብነው ቀረና ግዜን ግዜ ተካ

በዘመን ፍጻሜ ሞተም አለ ለካ

እማምዬ የሁሉ እናት

 

እህት አለም ቆንጅት ወንድም አለም መስፍን

ቁም ነገር ስለሺ አኩሪያችን ለወገን።

እህት አለም ቹቹ ወንድሜ ኤልያስ ውለታ አክባሪው

ወርቅ አበባ እህቴ ትዕግስት ባንቺ ነው

ፍሬህይወት አደራ እናት ነሽ ለሁሉ

አንዳርጋቸው ሰብሰብ እንጸልይ በሉ

የአጸደ ማርያም ነፍሷን ይማር በሉ

ለአልማዝ ሀሌማ ነፍሷን ይማር በሉ።

ለአልማዝ ሀይሌማ ምንድን ነው ማልቀስ

ጥቁር ከል መልበስ ከወዴት ሊያደርስ

በሀይማኖት ጸንታ ላረፈችው ነፍስ።

እግዚአብሄር ነውና ደግ ሰው አክባሪ

በቸር ተቀብሎ ያኑርሁ ፈጣሪ

ደህና ይሰንብቱ የኔ አልማዝ ሀይሌ

ፍቅሬ እመቤቴ

እርስዎን አልረሳሁም እስክታልፍ ህይወቴ

                 ----------------------------------------

 

 

የመድኀኔዓለም፡እህትማማቾ

ለአባላቸው፡ለወይዘሮ፡አልማዝ፡ኃይሌ፡ያቀረቡት።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

                              

I

የመድኀኔዓለም ፡  አንጋፋዉ ፡ ማሕበር ፤

ይደምቅ ፡ ነበር ፡ ባንቺ ፡ እዚህ ፡ መኖር ።

 

በድንግል ፡ ማርያም ፡ እያገለገለች፣

ከልጅ ፡ ከአዋቂው ፡ ጋር ፡ በፍቅር ፡ እየኖረች ፣

ደጎ ፡ እህታችን ፡ አልማዟ ፡ ነበረች ።

 

ሕመሟ ፡ ተሰምቶ ፡ መቼ ፡ ተጠየቀች ፤

እንዲያው ፡ ባጭር ፡ ጊዜ ፡ ለመጟዝ ፡ ቸኮለች ።

 

አንቺ ፡ ሁሉንም ፡ ነው ፡ የምታጎርሽው ፤

አንቺ ፡ ሁሉንም ፡ ነው ፡ የምትዳብሽው፤

ቢተረክ ፡ አያልቅም ፡ ሰው ፡ ቢናገረው ።

 

ደግነት ፡ ለራስ ፡ ነው፡ እንዳቺም ፡ ባይበዛ፤

እንዴት፡ ትሔጃለሽ፡ እንዴህ፡ እንደዋዛ ።

 

እኛ፡ እንሙትልሽ፡ አንቺ፡ አትሙችብን፤

ፈትፍቶ፡ እሚያጎርሰን፡ እጅሽ፡ ተያዘብን ።

 

በእጅጉ፡ ተጎዳን፡ ማሕበረተኞችሽ፤

በድንጘት፡ ሆነና፡ ከኛ፡ መለየትሽ ።

 

የማይቀር፡ ለሁሉ፡ ሞት፡ የሚሉት፡ ጣጣ፤

ቀንዋ፡ ደረሰና፡ እጣው፡ በሷ፡ ወጣ።

 

አንቺ፡ ስትለይን፡ አዘነ፡  ልባችን፤

ደግነትሽ፡ ቀርቶአል፡ ከመካከላችን።

 

አመሏ፡ ለስላሳ፡ ከማር፡ ከወተት፤

እንደምን፡ ጨክኖ፡ እሷን፡ ወሰዳት።

 

የእናት፡ ማሕበረተኛ፡ የእህት፡ ማሕበረተኛ፤

ድንገት፡ ተለየችን፡  አጎደለች፡ ለኛ።

 

ልጅ፡ አትል፡ አዋቂ፡ ሕጻን፡ ሽማግሌ፤

ለሁሉም፡ እኩል፡ እናት፡ ወ/ሮ፡ አልማዝ፡ ኃይሌ።

 

በማርያም፡ ግቢ፡ ውስጥ፡ የተከልሽው፡ ተክል፤

አብቦአል፡ አፍርቷል፡ አንቺን፡ ሊወክል።

 

አበባው፡ አብቦ፡ ባየነው፡ ቁጥር፤

“የአልማዝዬ፡ ተክል”፡ እንለው፡ ጀመር።

 

ማሕበረተኞሽ፡ ሁሉ፡ አዘኑ፡ አለቀሱ፤

እግዚአብሔር፡ ፈልጞ፡ ወሰደሽ፡ ለራሱ።

 

የተናገርሽውን፡ ሁሉ፡ ፈጽመናል፡

ከበሮ፡ መዝሙሩ፡ ሽብሸባው፡ ነጩንም፡ ለብሰናል፡

ቀና፡ ብለሽ፡ ብታይ፡ እንዴት፡ ደስ፡ ይለናል።

 

ከአምላኳ፡ ጋር፡ የተነጋገረች፣

ቃሉን፡ በሚገባ፡ ጠንቅቃ፡ ያወቀች፣

ፈጣሪዋን፡ ፈሪ፡ ደግ፡ ሰው፡ ነበረች።

 

መድኀኔዓለም፡ በቀኝ፡ ሚካኤል፡ በግራ፣

ነፍስሽን፡ ያኑሩት፡ ከነአብርሃም፡ ጋራ።

                       -------------------------------------------------------------

.

bottom of page