top of page

የአልማዝዬ የ፹ኛ ዓመት ንግግር.

በስመ፡አብ፡ወወልድ፡ወመንፈስ፡ቅዱስ፡አሀዱ፡አምላክ፡አሜን። ምንም፡በተለያየ፡ጊዜ፡ኃዘነና፡መከራዬ፡ሁሉን፡ቻይ፡አምላክ፡እንደምችለው፡አድርጎ፡ሰጥቶኝ፣ሁሉም፡በጊዜው፡አልፎ፡አሁን፡ከኃዘኑ፡ዘመን፡የደስታው፡ዘመን፡በልጦ፡አግኝቼዋለው።የመደኃኔዓለም፡ስጦታ፡ተነግሮ፡አያልቅም። እኔ፡በግማሽ፡እድሜዬ፡የዛሬ፡አርባ፡አመት፡ሞቼ፡ቢሆን፡ኖሮ፣ኃዘኔም፡እንደቆጨኝ፣ኃጢአቴም፡እንደኮሰከሰኝ፡በሆነ፡ነበር።ነገር፡ግን፡የኔ፡መደኃኔዓለም፡ቆይ፡የምትፀናኚበት፡መንገድ፡አለ፡ብሎ፡ለኔ፡የደስታ፡ዘመን፡ጨመረልኝ።በልጆቼም፡አስደሰተኝ።ልጆቼንም፡ለበረከት፡አቀረበልኝ።ሁሉም፡ደግና፡ርህሩህ፡ናቸው።በእዉነቱ፡ከሆነ፡እኔ፡ስለልጆቼ፡ጥሩነት፡ያለዛሬ፡በሙሉ፡አፌ፡ተናግሬው፡አላውቅም።ለመናገርም፡እፈራለው።ምክኒያቱም፡ከንቱ፡ውዳሴ፡እንዳይሆንብኝ፡ብዬ፡ነበር።አሁን፡ግን፡በዚህ፡እድሜ፡በሆዴ፡ውስጥ፡እንደታመቀ፡እንዳላልፍ፡መናገር፡ግድ፡ሆነ።እግዚአብሔር፡ምንም፡ሳላደርግለት፡እኔን፡እንዲህ፡አድርጎ፡በልጅ፡ትሩፋት፡መሙላት፡በጣም፡ያስደንቀኛል።አምላክ፡የቸርነቱን፡ስራ፡ሲሠራ፡ክፉንና፡ደግን፡ለይቶ፡አይደለም።የፈጠረውን፡ሁሉ፡ይወዳል።ስሙ፡ለዘላለም፡የተመሰገነ፡ይሁን።ድሮ፡በአምስትና፡ስድስት፡ሠራተኛ፡ነበር፡የኖርኩት።ይገርማችኃል፣እኔ፡አሁንም፡ብዙ፡ሠራተኞች፡አሉኝ።እነሱም፡ልጆቼ፡ናቸው።አምላኬን፡በዚህ፡ስለባረከኝ፡በጣም፡አመሰግነዋለሁ።እኔ፡በምርቃት፡ስለማምን፣እባካችሁ፡ልጆቼን፡መርቁልኝ። እኔ፡እንደ፡ኢትዮዽያ፡አቆጣጠር፡ነሐሴ፡12,1926፡ዓመተ፡ምህረት፣ከእለቱ፡ወደማታ፡ሲሆን፡አዲስ፡አበባ፡ከተማ፡ላጋር፡አካባቢ፡ተወለድኩ። አባቴ፡በጅሮወንድ፡ኃይሌ፡ጎልማሜ፡እናቴ፡ወይዘሮ፡ወርቅአበባ፡ወርዶፋ፡ይባላሉ። አባቴ፡ከህፃንነት፡እስከ፡እውቀት፡እንደልጃቸው፡ያሳደጏቸውና፡ያስተማሯቸው፡ራስ፡ብሩ፡ወልደገብርኤል፡ነበሩ። እኔም፡በተወለድኩበት፡ዘመን፡የራስ፡ብሩ፡አማካሪና፡የራስ፡ብሩ፡ቤትና፡ንብረትን፡በተመለከተ፡በተግባር፡ፈፃሚ፡እሳቸው፡ነበሩ።በዚህ፡የተነሳ፣ራስ፡ብሩ፡በተሾሙም፡ሆነ፡በተጋዙ፡ጊዜ፡አባቴ፡አብረው፡መሄድ፡ነበረባቸው። እኔ፡በተወለድኩኝ፡በአርባ፡ቀኔ፣ራስ፡ብሩ፡ተግዘው፡ወደ፡አሩሲ፡በሄዱ፡ጊዜ፡የአባቴ፡አብሮ፡መሄድ፡ግድ፡ስለነበር፣በእድሜ፡በጣም፡ወጣትና፡አራስ፡የሆነችሁን፡ባለቤታቸውን፡ወደወላጆቻቸው፡ላኩ። በዚያ፡ጥቂት፡ወራቶች፡እንደቆየን፡አባቴ፡ስለተመለሱ፣እናቴና፡እኔ፡ወደ፡አዲስ፡አበባ፡ተመለስን። አሁንም፡ብዙም፡ሳይቆይ፡ጣልያን፡ኢትዮዽያን፡ወረረች።በመጋቢት፡1928፡አባቴ፡ራስ፡ብሩን፡ተከትለው፡ማይጨው፡በዘመቱ፡ጊዜ፡እኔ፡የአንድ፡አመት፡ልጅ፡ስሆን፡እናቴ፡ወንድሜን፡አበራ፡ኃይሌን፡ነፍሰጡር፡ነበረች። በማይጨው፡ዘመቻ፡እናቴ፡ባለቤቷ፡ብቻ፡ሳይሆኑ፡አባቷም፡ቀኛዝማች፡ወርዶፋ፡ዘምተው፡ስለነበር፡አዲስአበባ፡መቆየት፡ነበረባት። አባቷ፡ቀኛዝማች፡ወርዶፋ፡የስመጥሩዉ፡ጀግና፡የደጃዝማች፡ገረሱ፡ዱኪ፡አጎት፡ነበሩ። አባቴ፡ከማይጨው፡ሲመለሱ፡አበራ፡ተወልዶ፡ጠበቃቸው። ከዚያም፡ራስ፡ብሩ፡ከጃንሆይ፡ጋር፡ስደት፡ስለሄዱና፡ከተማውም፡ስለተሸበረ፣አባቴ፡እናቴን፡እኔንና፡አራስ፡የሆነውን፡ወንድሜን፡ይዘው፡ወደ፡ምሁር፡መሄድ፡ፈለጉ።ሆኖም፡የሚያስፈልገውን፡መሰንዶ፡ለማድረግ፡በቅድሚያ፡ብቻቸውን፡መሄድ፡ስለፈለጉ፡ለጊዜዉ፡እንደገና፡ወደ፡አባቷ፡መኖሪያ፡ወደ፡ቆራ፡ወሰዱን። እናቴ፡አባቷ፡ከማይጨው፡ተመልሰው፡በዚያ፡አገኘቻቸው። እኛ፡ቆራ፡ሆነን፡ለጥቂት፡ጊዜ፡ብሎ፡የሄዱት፡አባታችን፡ሳይመለሱ፡ብዙ፡ቆዩ።ጊዜው፡የግርግር፡ጊዜ፡ነበር።አባታችን፡አስፈላጊውን፡መሰንዶ፡ጨርሰው፡በሚመለሱበት፡ወቅት፣በጉራጌና፡በአድያ፡ብሀረሰቦች፡መሀል፡ግጭት፡ስለተፈጠረ፡መንገድ፡በመዘጋቱ፡የተነሳ፡ማለፍ፡አቃታቸው።ሆኖም፡ግን፡ይህ፡በአባታችን፡ላይ፡የተከሰተው፡ችግር፡እኛ፡ባለንበት፡አካባቢ፡ወሬው፡ስላልደረሰ፣የአባታችን፡ሄዶ፡መቅረት፡የእናቴን፡አባት፡ብስጭት፡ላይ፡ከተተ።በዚህ፡ጊዜ፡ጣልያን፡አያቴ፡በነበሩበት፡ከተማ፡መግባት፡ብቻ፡ሳይሆን፡አያቴ፡ወደ፡ጣልያን፡እንዲገቡ፡ሊያባብላቸው፡ይሞክር፡ነበር። እሳቸው፡ግን፡ወንድሞቻቸው፡ከሆኑት፡ከእነ፡ደጃዝማች፡ገረሱ፡ዱኪ፡ጋር፡ጫካ፡ገብቶ፡ለመዋጋት፡ይዘጋጁ፡ነበር። ሆኖም፡እናቴን፡እና፡እኛን፡ለጣሊያን፡ትቶ፡ጫካ፡መግባት፡ሊያስከትለዉ፡የሚችለዉን፡መዘዝ፡በመፍራት፡በነገሩ፡ያስቡበትና፡የከተማውን፡ሽማግሌዎች፡ያማክሩበት፡ጀመር።ይህ፡በእንዲህ፡እንዳለ፣ብዙ፡ጊዜ፡አባብሎ፡ያቃተው፡ጣሊያን፡በንዴት፡ይተናጎላቸው፡ጀመር።በመሬታቸው፡ላይ፡ቀን፡የሚያስተክሉትን፡ዛፎች፡እና፡ችግኞች፡የራሱን፡ሰዎች፡እየላከ፡ያስፈርስባቸዋል።በቂ፡ጊዜ፡ከታገሱ፡በኃላ፡ልጃቸውን፡እናቴን፡ለሌላ፡ሰው፡በመዳር፡እኛንና፡እናታችንን፡በማትረፍ፣እሳቸው፡በአርበኝነት፡ለመዋጋት፡ቆረጡ።እዚያውም፡እናቴ፡አባቴን፡ከማግባቷ፡በፊት፡ለጋብቻ፡ጠይቀው፡የነበሩት፡አቶ፡ንጋቱ፡ደስታ፡በዚያው፡አካባቢ፡ስለተገኙ፡ስለጉዳዩ፡ተጠየቁ።እሳቸውም፡ያለምንም፡ማንገራገር፡ስለተስማሙ፡ሰርግ፡ይደገሳል።ለሠርጉ፡ዋዜማ፡ዳስ፡ተጥሎ፡እየተጨፈረ፡እየተዘፈነ፡እያለ፣የወላጅ፡አባቴ፡ሁለት፡ወንድሞች፡ከሌሎች፡አራት፡አሽከሮች፡ጋር፡ስድስት፡በቅሎዎች፡ይዘው፡ከአባቴ፡ተልከው፡እናቴንና፡እኔና፡ወንድሜን፡ለመውሰድ፡መጡ።የደረሱት፡ለሠርጉ፡ዋዜማ፡ስለነበር፣ሠርጉን፡ተመልክቶ፡ባዶ፡እጃቸውን፡ከመሄድ፡በቀር፡ሌላ፡ምንም፡ምርጫ፡አልነበራቸውም።ከሠርጉ፡በኃላ፡አያቴ፡ቀኛዝማች፡ወርዶፋ፡ለእናቴ፡አዲስ፡ባለቤት፡ለአቶ፡ንጋቱ፡እርጥብ፡ሣር፡ነጭተው፡በምድር፡የሰጠሁህን፡በሰማይ፡እቀበልሀለው፡ብለዋቸው፡እርሳቸው፡ከሌሎች፡ወንድሞቻቸዉ፡ከሆኑት፡ከነደጃዝማች፡ገረሱ፡ጋር፡በአርበኝነት፡ለመዋጋት፡ጫካ፡ገቡ። ከዚያ፡በኃላ፡እኛም፡ከአዲሱ፡አባታችን፡ጋር፡መኖር፡ጀመርን።በጣም፡ትሁትና፡ደግ፡አባት፡ነበሩ።እኔንና፡አበራን፡በጣም፡ይወዱን፡ነበር።ወደ፡አዲስ፡አበባ፡በሄዱ፡ቁጥር፡ልብስ፡ይዘውልን፡ይመጡ፡ነበር።እናታችንንም፡በጣም፡አክብረው፡ይዘዋት፡ነበር።እንግዲህ፡እኔና፡ወንድሜ፡ነፍስ፡ስናውቅ፡የማናውቀው፡አባታችን፡አባባ፡ንጋቱን፡ነበር።በዚህ፡ሁኔታ፡እየኖርን፡ሳለን፡በመሀል፡አባቴ፡ባለቤታቸውን፡ስለተቀሙ፡በአቶ፡ንጋቱ፡ላይ፡ክስ፡መሰረቱ።ክሱ፡በጣሊያን፡ፍርድ፡ቤት፡ሆኖ፡በአቅራቢያዉ፡በሚገኘው፡በወሊሶ፡ከተማ፡ነበር።በቀጠሮው፡ዕለት፡ሁላችንም፡ወደ፡ወሊሶ፡ሄድን።ከቤት፡ስንወጣ፡ቤተሰቡ፡ያለቅስ፡ነበር።አባባ፡ንጋቱም፡አይናቸው፡እንባ፡አቅርሮ፡በሀዘን፡ይመለከቱን፡ነበር።እኛ፡ግን፡ምን፡እንደሆነ፡ነገሩ፡አልገባንም፡ነበር።ከፍርድ፡ቤት፡ስንደርስ፡ፍርድ፡ቤቱ፡በሰው፡ሞልቶ፡ነበር።እናታችንና፡አቶ፡ንጋቱ፡እኛን፡ከውጪ፡አስቀምጠውን፡እነሱ፡ወደ፡ውስጥ፡ገቡ።አባባ፡ንጋቱም፡አልፎ፡አልፎ፡እየወጡ፡ያዩንና፡ከኪሳቸው፡ከረሜላ፡እያወጡ፡ይሰጡናል።ጥቂት፡ጊዜ፡እንደቆየን፡አንድ፡አለባበሱ፡በጣም፡ያማረ፡በጣም፡መልከመልካም፡የሆነ፡ምን፡አልባትም፡የሀያ፡ሰባት፡ወይንም፡የሀያ፡ስምንት፡አመት፡እድሜ፡የሚሆነው፡ጎልማሳ፣ሰው፡ሁሉ፡እንኳን፡ደስ፡ያለህ፡እየተባለ፡ከውስጥ፡ወጣና፡እኔንና፡ወንድሜን፡እያገላበጠ፡ሳመን።ከእሱ፡ጋር፡የነበሩት፡ሰዎችም፡አባታችሁ፡ኃይሌ፡ነው፡ሲሉን፡አባታችን፡ንጋቱ፡ነው፡እያልን፡ማልቀስ፡ጀመርን።በኃላ፡እንደሰማሁት፣ፍርድቤቱ፡ለእናታችን፡ምርጫ፡ሰጥቶ፡እሷ፡አዲሱን፡ባሏን፡ስለመረጠች፣ለወላጅ፡አባታችን፡ልጆቹ፡ተፈረደውለት፡ስለነበረ፡ነው።ሆኖም፡እኛን፡መውሰድ፡ቀላል፡ጉዳይ፡አልነበረም።አንሄድም፡ብለን፡አስቸገርን።ከብዙ፡ማግባባት፡በኃላ፡በመጀመሪያ፡ወንድሜን፡አባብለዉ፡ወሰዱት።በማግስቱ፡ወንድሜ፡በአዲስ፡ሱፍ፡ልብስ፣አዲስ፡ጫማና፡ባርኔጣ፡አሸብርቆ፡መጣ።ከዚያ፡ለእኔም፡ይደረግልሻል፡ተብዬ፡ተወሰድኩኝ።የሚያብለጭልጭ፡ጌጥ፡ልብስና፡ጫማ፡ተገዛልኝ።ከዚያ፡በዚህ፡ሰበብ፡እንደወጣን፡ከእናታችን፡ተለየን።እኔ፡እናቴን፡በጣም፡እወድ፡ነበር።አባታችን፡መኪና፡ተከራይተው፡ይዘውን፡ወደ፡ወልቂጤ፡ሄዱ።እኔም፡እንዳለቀስኩኝ፡ከዚያ፡ደረስን።እዚያ፡አባቴ፡ከእናቴ፡በፊት፡ወልዷቸው፡የነበሩትን፡ሁለት፡እህቶቻችንን፡ተዋወቅን፣ተገናኘን።ወልቂጤ፡ብዙ፡ልጆች፡ነበሩና፡ከጨዋታ፡ብዛት፡ትንሽም፡ቢሆን፡ማልቀሱ፡ቀረ።በወልቂጤ፡እያለን፡ጣልያን፡ከኢትዮዽያ፡የሚወጣበት፡ጊዜ፡ደረሰ።ትልቅ፡ውጊያም፡ስለነበረና፡አውሮፕላን፡ቦንብ፡ይጥል፡ስለነበረ፣ቀን፡ቀን፡ወደ፡ጫካ፡እየወሰዱን፡እዚያ፡እንውል፡ነበር።አውሮፕላንም፡በሚያንዣብበትም፡ጊዜ፡እኛን፡በሆዳችን፡እያስተኙ፣እነሱ፡በላያችን፡ላይ፡ሲሆኑ፡ትዝ፡ይለኛል።ከዚያም፡የጃንሆይ፡መግባት፡ስለተሰማ፡አባታችን፡ራስ፡ብሩን፡ለመገናኘትም፡ጭምር፡ወደ፡አዲስአበባ፡ሄዱ።ከጥቂት፡ጊዜ፡በኃላም፡አውቶሞቢል፡ይዞ፡መጥቶ፡ወደ፡አዲስአበባ፡ጉዞ፡ጀመርን።ከዚያም፡በእግረመንገዳችን፡ከእናቴ፡መንደር፡ቆምን።የእናቴ፡አክስት፡በመንገዱ፡ዳር፡ነበርና፡የሚኖሩት፣እሳቸውን፡ሊያሳየን፡ከመኪና፡ወረድን።አክስቴን፡ከአገኘን፡በኃላ፣አክስታችን፡አባታችንን፧እባክህ፡እኔ፡ጋር፡ተዋቸውና፡እናታቸውን፡እንዲያዮ፡ይሁን፧እኔ፡በቅርቡ፡አዲስ፡አበባ፡ስለምመጣ፡ይዣቸው፡እመጣለሁ፣ቢሉት፥የለም፡በቅርቡ፡ደጃዝማች፡ገረሱ፡አገር፡ለማቅናት፡ወደ፡ወላሞ፡ይሄዳሉን፡ስለሰማሁና፤እሷም፡አብራ፡ልትሄድ፡ስለምትችል፡ይዛብኝ፡ትሄዳለች፡ብለው፡ፍራቻቸውን፡ገለፁላቸው።በኃላ፡ግን፡ይህ፡እንደማይሆን፡ስላሳመኑት፡እሺ፡አለ።አሁን፡ወንድሜ፡ከአባቴ፡አልለይም፡ብሎ፡ስላስቸገረ፡ቀረ።እኔ፡ግን፡ያቺ፡የናፈቀችኝን፡እናቴን፡ለማየት፡ቀረሁ።እናቴን፡አገኘኃት።አባባ፡ንጋቱንም፡አገኘዋቸው።በጣም፡በደስታ፡ተቀበሉኝ።መቆየት፡የነበረብኝ፡ሦስት፡ቀን፡ብቻ፡ነበር።ነገር፡ግን፣ናፍቆታችን፡እንደዚህ፡በቀላሉ፡የሚያልቅ፡ስላልነበረ፡መመለስ፡በሚገባኝ፡ቀን፡ምክኒያት፡እየተፈጠረ፡ሳልሄድ፡ቀረሁኝ። ጥቂትም፡ቆይተን፡እንደተፈራው፡ደጃች፡ገረሱ፡ወላሞን፡ለማቅናት፡በሄዱ፡ጊዜ፡ዘመዶቻቸውን፡ሁሉይዘው፡ስለሄዱ፡እናቴም፡እኔን፡ይዛ፡ከባለቤቷ፡ጋር፡አብራ፡ሄደች።አባቴ፡የፈራውም፡ደረሰ።በዚያ፡ጊዜ፡እድሜዬ፡ለትምህርት፡ደርሶ፡ነበርና፡በወላሞ፡በሚገኝ፡ዘመናዊ፡ትምህርት፡ቤት፡ገባሁኝ።ከዚያም፡ደጃች፡ገረሱ፡ወደ፡ጎሙጎፋ፡ሲዛወሩ፡አሁን፡አርባ፡ምንጭ፡ያኔ፡ደግሞ፡ጬንቻ፡ተብሎ፡ይጠራ፡በነበረበት፡ከተማ፡ትምህርቴን፡ቀጠልኩኝ።ደጃዝማች፡ገረሱ፡በየሄዱበት፡ትምህርትን፡ለማስፋፋት፡ምኞት፡ስለነበራቸው፡ወዲያው፡አስተማሪና፡አስፈላጊዉ፡ሁሉ፡ተሟልቶ፡ትምህርት፡ቤት፡ይከፈት፡ነበር።እኔም፡ሁልጊዜ፡የእድሉ፡ተካፋይ፡እሆን፡ነበር።አሁንም፡ጥቂት፡አመታት፡እንደቆየን፡እናቴ፡እኔን፡ይዛ፡ወደ፡አዲስአበባ፡ሄድን።ወስዳም፡ለወላጅ፡አባቴ፡አስረከበችኝ።ከእናቴ፡ጋር፡እንደገና፡ተለያየን።አሁን፡አደኩኝ።በአእምሮም፡ጎለመስኩኝ።ከአባቴ፡ሳልለይ፡ትምህርቴን፡ተከታተልኩኝ።በአሥራ፡ሦስት፡አመቴ፣የአሥራ፡አንድ፡አመቱ፡ወንድሜ፡በሞት፡ተለየን።ለመላዉ፡ቤተሰብ፡ምሩር፡ሀዘን፡ሆነ።አሥራ፡ስምንት፡አመት፡ሲሞላኝ፡በ1945 ዓመተ፡ምህረት፡አባቴ፡ይወደዉ፡ለነበረው፡ለልጆቼ፡አባት፡ለልጅ፡ሻውል፡ገብረ፡መስቀል፡ዳረኝ።ባለቤቴ፡በደግነቱና፡በርህሩህነቱ፡የታወቀ፣ቆንጆ፡የደም፡ግባት፡ያለው፡ቤተሰቡን፡በጣም፡የሚወድ፡ሰው፡ነበር።ከጋብቻዬ፡ከአንድ፡አመት፡በኃላ፡ያቺ፡የምወዳት፡እናቴ፡በድንገት፡ሞተችብኝ።ከባለቤቴ፡ጋር፡አሥራ፡ስምንት፡አመት፡አብረን፡ኖረናል።አብረን፡በኖርንበትም፡ዘመን፡ስምንት፡ልጆችን፡አፍርተናል።ባለቤቴ፡በ1963፡ዓመተ፡ምህረት፡ሐምሌ፡አንድ፡ቀን፡ከዚህ፡አለም፡በሞት፡ሲለየኝ፡የአርባ፡ስድስት፡አመት፡ሰው፡ነበር። ይህ፡ደግ፡አባት፡ልጆቹን፡ሳይጠግብ፡በሞተ፡ጊዜ፡እኔ፡የሰላሣ፡ስድስት፡አመት፡ሴት፡ነበርኩኝ።ቤተሰቡ፡ብዙ፡ነበር።ከወለድኳቸው፡ልጆች፡ሌላ፡የሚያድጉ፡ብዙ፡ልጆች፡ነበሩ።ባለቤቴ፡ከመሞቱ፡በፊት፡ሁሉንም፡ነገር፡የሚያደርገው፡እሱ፡ስለነበረ፣ከእሱ፡እረፍ፡በኃላ፡ኑሮን፡ማስተካከሉና፡መምራቱ፡ቀላል፡አልነበረም።ከሦስት፡አመት፡በኃላ፡በ1966፡አብዮት፡ጊዜ፡ኃይለኛው፡ችግር፡መጣ።ቤተሰቦቼን፡አስተዳድርበት፡የነበረው፡የገጠር፡እርሻ፡መሬትና፡የከተማ፡የኪራይ፡ቤቶች፡ሁሉ፡ተወሰዱ።ኑሮ፡በጣም፡ከበደ።በዚህ፡ጊዜ፡የመጀመሪያዎቹ፡ሁለት፡ልጆቼን፡ወደ፡አሜሪካን፡ልኬ፡ነበር።የቀሩትን፡ልጆቼን፡በግል፡ትምህርት፡ቤት፡ማስተማርና፡በእንክብካቤ፡ለማሳደግ፡አገኘዉ፡የነበረው፡ፈተና፡እና፡ችግር፡ቀላል፡አልነበረም።በ1969፡ዓመተ፡ምህረት፡ሁለተኛዋን፡ሴት፡ልጄን፡ፍሬሕይወት፡ሻውልን፡ዳርኩኝ።በዚሁ፡ጊዜ፡ደርግ፡ወጣቶችን፡የሚጨርስበት፡ጊዜ፡ነበር።ሌላው፡ልጄ፡መስፍን፡ገና፡አፍላ፡ጎሮምሳ፡ስለነበር፡ከአሁን፡አሁን፡ይገልቡኛል፡በማለት፡ጭንቀቴ፡በጣም፡ከባድ፡ነበር።መስፍን፡ምንም፡እንኳን፡በኃላ፡ተይዞ፡በወቅቱ፡ወጣቱን፡ይጨርሱ፡በነበሩት፡የደርግ፡ካድሬዎች፡እጅ፡ቢወድቅም፣እግዚአብሄር፡በነሱ፡ፊት፡ሞገስን፡እንዳገኝ፡አደረገ።የሚገርመዉ፡እነዚያ፡ገዳዮች፡እነዚያ፡ለአካባቢዉ፡ወጣት፡እልቂት፡ምክኒያት፡የሆኑ፡ጨካኞች፡ለእኔ፡ያላቸዉ፡ክብር፡መጠን፡የለውም።እኔ፡እግዚአብሄር፡ምስክሬ፡ይሆናል፡ምንም፡ነገር፡አድርጌላቸው፡አላውቅም፡እንዲሁ፡ጥሎባቸው፡ይወዱኛል።መስፍን፡በታሰረ፡በአስራ፡አምስተኛው፡ቀን፡ይዘውት፡አመጥተው፡ከቤቱ፡አሰሩት።ከዚያ፡ሁሉ፡እሳት፡አውጥተው፡በራሱ፡ቤት፡ለሦስት፡ሳምንት፡ካሰሩት፡በኃላ፡በነፃ፡ለቀቁት።መስፍንን፡ከአገር፡አስወጥቶ፡ወደ፡አሜሪካን፡ለመላክ፡ያየሁት፡አበሳ፡የሚረሳ፡አይደለም።ኢሚግሬሽን፡ተዘግቶ፡ወጣት፡እንዳይወጣ፡በተከለከለበት፡ጊዜ፡ነበር፡የኔ፡መድኃኔአለም፡ፍቃዱ፡ሆኖ፡ለመስፍን፡እንዲፈቀድለት፡ያደረገው።በ1973፡በነሐሴ፡አባቴ፡በጅሮወንድ፡ኃይሌ፡ጎልማሜ፡በሞት፡ተለዮኝ።ወላጅ፡አባቴ፡ሁልጊዜ፡በችግሬ፡ጊዜ፡ያለተለዮኝ፡ደጋፊዬ፡ነበሩ።መስፍን፡ወደ፡አሜሪካን፡ከመጣ፡ከስድስት፡አመት፡በኃላ፡ትንሹ፡ልጄ፡ስለሺ፡ትምህርቱን፡ሲጨርስ፡ልጆች፡ወደ፡ውትድርና፡የሚላኩበት፡ጊዜ፡ነበር።ስለሺ፡ሦስት፡በተለያየ፡ጊዜ፡ከቤቱ፡በሌሊት፡እየመጡ፡ወስደውት፣ሦስቱንም፡ጊዜ፡ሌሎች፡አብረውት፡የተወሰዱ፡ወጣቶች፡ሲሄዱ፡እግዚአብሄር፡በየምክኒያቱ፡ያስቀረዉ፡እድለኛ፡ልጄ፡ነው።አንዴ፡የማልረሳው፡የአካባቢው፡ወጣቶች፡ወደ፡ውትድርና፡ለመሄድ፡በሚታፈሱበት፡ሰሞን፡በጣም፡ከመጨነቄ፡የተነሳ፡ወደ፡ባልቻ፡ሆስፒታል፡ወስጄ፡ልጄን፡አሞታል፡ብዬ፡እንዲያስተኙት፡አደረኩኝ።ዋናው፡አላማዬ፡ነገሩ፡እስኪያልፍ፡ድረስ፡ስለሺን፡ለማሸሽ፡ነበር።በጣም፡የሚገርመው፡ሆስፒታል፡አሥራአምስት፡ቀን፡አስተኝቼው፡ከሆስፒታልየወጣ፡ቀን፡ማታ፡መጥተው፡ወሰዱት።እግዚአብሄር፡ግን፡ነውና፡እንዳይሄድ፡አድርጎታል።እኔ፡ከዛሬ፡ሀያ፡ስድስት፡አመት፡ጀምሬ፡ከልጆቼ፡ጋር፡ስኖር፡እገኛለሁ።በዚህ፡26፡አመት፡ዘመን፡የመጀመሪያዋን፡ልጄን፡ገበያነሽ፡ሻውልን፡አጥቻለው።ከዚያ፡በተረፈ፡ልጆቼ፡እየተቀባበሉ፣እየተንከባከቡ፡ይዘውኛል።እኔ፡ያለልጆቼ፡አገር፡የለኝም።በመጨረሻ፡ይህን፡በዓል፡ለእኔ፡ደስ፡በሚለኝ፡አኳኃን፡አስባችዉ፡ስላዘጋጃችው፡መድኃኒአለም፡ቤታችሁን፡ያዘጋጅላችው።ንብረታችሁን፡በበረከት፡ይሙላ።ብዙ፡ተባዙ፣በልጆቻችሁም፡ተደሰቱ።የኔንም፡እድሜ፡ይስጣችሁ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ከወርቅአበባ ሻውል

፹ኛ  ዓመቷን ስታከብር የተገጠመ ግጥም

 

ፍቅረ ምስክር

ተመስገን ጌታዬ ለዚህ ላበቃኸኝ

ፍቅርን ለመመስከር በሕይወት አቆየኸኝ

ፍቅሬ እማምዬ እንኳን አደረሰሽ

ፍቅረ ምስክር ነው የልደት ስጦታሽ።

 

ከየት ብዬ ልጀምር የእምማምዬን ሕይወት

ታሪኳን አውቃለሁ ከትውልዴ በፊት

ስላጫወተችን ታሪኳን ዘርዝራ

ተቀርጿል እንደ ፊልም እሷ ስታወራ

በሁላችን አንጎል በእያንዳንዳችን

የፍቅር መጽሐፍ ታትሟል ብርሃን።

ብሩህ ነው ድንቅ ነው ያኮራናል እኛን

እንዲህ ትለን ነበር ታሪኳን ስትነግረን:

 

“ተቀጽላ ስሜ ነበረ ጦጢት

ብልጥ ስለነበርኩ ስለማውቅ ብልሃት

ጣልያን እንደሄደ ከአምስት አመት ግዛት

በኢትዮጵያ ታወጀ ስልጣኔና መብት

ጃንሆይም አዘዙ ደጃዝማች ገረሱን

ሀገር እንዲያቀኑ እንዲያስፋፉ እውቀትን

ደጃዝማች ገረሱ ስመ ጥሩ አርበኛ

ነበሩ የእናቴ ዘመድም ጓደኛ

ጓዝና ስንቅ ይዘው ለመሄድ ሲነሱ

በዘመድ መታጀብ ወደዱ ገረሱ

እኔና እናቴም ተከትለን ሄድን

ጋራ ሸንተረሩን ሀገርን አቋርጠን

 

ከብዙ ትዝታ አንዱ የማልረሳው

የትምህርትን ጥቅም በሚመለከተው

ብዙ ገጽ ግጥም ተፅፎ በአንድ ሰው

ቃላት ተስተካክሎ ላጠና ተሰጠኝ

በአደባባይ ላነብ ጦጢት ተመረጥኩኝ።

 

ጊዜ አልፈጀብኝም በቃሌ ሳውቀው

ብዙውን ገጽ ግጥም ስሸመድደው

ከግጥሙ መሃል የማይረሳኝ

የመጨረሻው ነው የሁለቱ ስንኝ

"ትንሿ ልጃችሁ ቃል ኪዳን ልገባ

የተማረ እንጂ  መሀይም ላላገባ"

እያልኩኝ በቃሌ ሁሉንም ሳወርደው

ሕዝቡ ተገረመ በጣም አስደነቀው

ተመሰጠ ከልብ ቀለጠ ጭብጨባው

ይህች ጦጢት አፍላ ገና ናት አበባ

 

 

 

አሉ ተጠንቀቁ ሰው አይን እንዳትገባ”

 

እያልሽ ስትነግሪን የልጅነትሽን

የትምህርቱ ወኔ በእኛም አደረብን

ላቅም ሄዋን ስትደርሺ ለአባታችን ተዳርሽ

በአምላክም ቸርነት ስምንት ልጆች ወለድሽ

ደጉ አባታችንን ሞት ቶሎ ወሰደው

ሕጻናቶች ሆነን ምኑንም ሳናውቀው

በጎልማሳነትሽ ተወጣሽው አንቺም

ልትሆኝልን ሁለት እናትም አባትም

 

ወዲያው ለውጥ መጣ ንብረት ተወረሰ

ፊትሽም በሃዘን ማድያት ለበሰ

አንድ የኛ ዘመድም መጣና መከረሽ

ከምትንገላቺ ብቻሽንም ሆነሽ

ችግር ከመጣና አንቺም ከደኸየሽ

ከግል ትምህርት ቤት ወደ መንግስት ይግቡ

ኑሮን እወቂበት አይኖችሽ አያምቡ

    አንቺ ግን የኛ እናት አልተዋጠልሽም

እርሱ ላንቺ ቢያዝንም አልተቀበልሽውም

እንደዚህም አልሽው ስትመልሺለት

በሕይወቴ እያለሁ እስካለኝም ጉልበት

የአምላክ ፈቃድ ሆኖ በእርሱ ቸርነት

አባታቸው እያለ ጥንት እንደነበረው

አንድም ሳይጓደል አልሽው አደርጋለው።

 

ወገብሽን ታጠቅሽ ልትሰዊ ፍቅርሽን

ጀግንነትሽ መጣ ቆራጧ እናታችን

ከዘመድ ከወዳጅ ብድር ተበድረሽ

ለጥቂት አመታት ልጆችሽን አስተማርሽ

ብድር እንደማይሆን አንቺም ተገነዘብሽ

ወንዷ እናታችን በኋላም ተነሳሽ

ንግድ ቤት ለመክፈት እቅድም አደረግሽ።

 

ነግዶ ለመብላት ልምዱም ባይኖርሽ

ለእኛ የነበረሽ ፍቅር አስገደደሽ

ንግዱንም ጀመርሽው ገብተሽ በሽርክና

ተማርሽ እማምዬ የንግድን ጎዳና

በኋላም አፈረስሽ የጋራዥ በርሽን

ዋርካ ምግብ ቤትን ከፈትሽ የራስሽን

ከብድርም ጫንቃ አንቺም ነጻ ወጣሽ

የውለታን አምላክ ጌታን አመሰገንሽ።

 

ቀላል አልነበረም የኢትዮዽያ ሕይወት

ስንቱን አሳለፈች እማዬ በእውነት

ፍዳዋን አየችው በቀይ ሽብር ጊዜ

የምንሞት መስሏት ሲገባት ትካዜ

አስታውሳለሁኝ ቀበሌ ታስረሽ

ለውትድርና ልጅ አምጪ ተብለሽ

በአንቺ የጸሎት ሀይል በፈጣሪ ስራ

አሜሪካን መጣን በተራ በተራ

ዘርዝሬ አልጨርስም እማዬ ፍቅርሽን

ሰው የሚማርከው ልዩ ፈገግታሽን

ምንኛ ታላቅ ነው የለጋስነትሽ

አንዴም ለእኔ ሳትይ ለእኛ በማሰብሽ

ከእኛ አልፎ ተርፎ የደግነትሽ ምንጭ

በኢትዮዽያ ደሀውም አለው ወር ተቆራጭ።

ሥራሽ የፍቅር ነው እናታችን ኩሪ

አንቺ አትጠገቢም ለዘላለም ኑሪ

እንኳን አደረሰሽ ለሰማንያ አመትሽ

የፍቅር ምስክር አበረከትኩልሽ።

 

 

የእዛቤል ንግግር ለእማዬ ልደት

 

እማዬ፣ ስላንቺ  ሳስብ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉትን ቅዱስ ሰዎች ታስታውሽኛለሽ።

 

        እንደ ዳዊት አንቺ  እንደዚህ አልሽ፥

        እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት        እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።

 

 አንቺ እንደ ሐና ፥

 

        ሌሊትና ቀን ከመቅደስ አትለይም፣ በጾምና በጸሎትም የምታገለግይ ነሽ።

 

እንደ ኢያሱሞ እንደዚህ ትያለሽ፥

        እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።

 

መጽሐፈ ምሳሌ ላይ እንደተጻፈላት ሴት አንቺ፥

        ምንም የሚጎድልብሽ ነገር የለም፥ በሕይወት ዘመንሽ ሁሉ።

        ለቤተሰቦችሽ አትሰጊም፤ በብርታትሽ ሞገስን ተጎናጽፈሻል።

        ከበሬታ ልብስሽ ነው፤ መጭውን ግዜይ በደስታ ትቀበያለሽ።
        አፍሽ በጥበብ ትከፈታለች፤ የርኅራኄም ሕግ በምላስሽ ትናገራለች።

        በአንደበትሽም ቀዕና ምክር አለ፤ ለቤተሰቦችሽም ጉዳይ በትጋት ተከታተያለሽ።

        ልጆችሽም እኛ እንነሣለን፥ ስናመሰግንሽ እንዲህ እንላለን።

        መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።
        እግዚአብሔርን ስለምትፈሪ የትመሰገነሽ ነሽ።

        ከእጅሽ ፍሬ እንስጥሻለን፥ ሥራዎችሽም በሸንጎ ይመሰገናሉ።

 

እማዬ አንቺ ልቤ፣ ነፍሴ፣ ሕይወቴ ነሽ። እኔና ልጆጆችሽ ለዘላለም እናከብርቫለን።

 

 

 

bottom of page