top of page

  የወይዘሮ  አልማዝ  ኃይሌ የትዉልድ ታሪክ

ከስለሺ ሻውል

 

እማምዬ ስለ ራሷ ሕይወት ስታወሳ ሁልጊዜ የምትጀምረው ከእናቷ የሕይወት ታሪክ ነው። ስለ እናትዋ አውርታ አትጠግብም። የእናትዋ በልጅነት ከዚህ ዓለም በሞት መለየት፣ ከነበራቸው የኑሮ ሁኔታ ጋር ተደምሮ ሁሌ ሲያንገበግባት ኖሯል። ሁልጊዜ የእናትዋ ሕይወት አለመሻሻልና፣ ሊኖራቸው ይገባው ለነበረው እንክብካቤ አለመሳካት የነበረችበትን ጊዜና ወቅት ስታማርር እናያት ነበር። ስለ እናቷ ስታወራ ለእናቷ ስለነበራት ፍቅር ለማወቅ በሞት ከአለፉ ከስልሳ አመት በኃላ እንባዋ በአይኗ ላይ ሲያቀር ብቻ ማየት ይበቃል። እንዴት አይነት ደርባባ ቆንጆና ትሁት ስለመሆናቸው ማውራት ትጀምርና፣ ተነስተውት የነበረውን እና በእጇ የተገኘውን ብቸኛውን የእናቷን ፎቶግራፍ በመመልከት<<ምናለ ቀና ብላ ተነስታ በሆነ ኖሮ>>ብላ ስትናደድ ትሰማለች። ፎቶግራፉ ለእማዬ ለመጀመሪያዋ ልጇ ለገባይነሽ ክርስትና የተነሱት ሲሆን ጉርድ ፎቶ ሆኖ ሕፃኗን ገባይነሽን ይዘዋት እሷን እያዮ ድንገት የተነሱት ነበር። ታዲያ ምንም የአይናቸው ቁልቁል ወደሕፃኗ መመልከት ልናየው የሚገባንን የአይናቸውን ውበት ቢከለክለንም ደርባባነታቸው እና የነበራቸው ግርማ ሞገስ በዚያ በአራት መዓዘን ተቀርፆ በቀረው ፎቶ ላይ ግልፅ ሆኖ ይታይ ነበር።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የእማዬ እናት ወርቅአበባ ወርዶፋ ይባላሉ። ትውልዳቸውም እንደሚከተለው ነው። የወይዘሮ ወርቅአበባ እናት ዘውዲቱ ማንደፍሮ የደጃዝማች ማንደፍሮ ልጅ ሲሆኑ፣ ደጃዝማች ማንደፍሮ ደግሞ ከደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ጦር አዛዦች ከፍተኛውን ቦታ ይዘው ከነበሩት አንዱ ነበሩ። የወይዘሮ ዘውዲቱ እናት ደግሞ ወይዘሮ ሙሉነሽ ጫጫ ሲሆኑ እሳቸውም የራስ ጎበና የጦር አበጋዝ የነበሩትና በታሪክም የታወቁት የደጃች ጫጫ ዶቢ ልጅ ናቸው። የእማዬ እናት ወይዘሮ ወርቅአበባ አባታቸውና እናታቸው በሕፃንነታቸው ተለያይተው ነፍስ ከወቁበት ጊዜ ጀምሮ የኖሩት ከአባታቸው ጋር ስለሆነ እናታቸውን ወይዘሮ ዘውዲቱን እምብዛም አያዉቁም። የእማዬን እናት ወይዘሮ ወርቅአበባን ወልደው ያሳደጏቸው አባታቸው ቀኛዝማች ወርዶፋ ጉልማ ሲሆኑ በምዕራብ ሸዋ ከሚገኘው አንጋፋ ከሆነው የኦሮሞ ክፍል የተወለዱ ናቸው። ይህ የኦሮሞ ክልል በጀግንነቱና በሀይለኛነቱ ከጥንት ጀምሮ የታወቀ ነበር። የቀኛዝማች ወርዶፋን ትውልድ ወደኃላ እስከ አሥራ ሰባት ድረስ የዘር ሀረጉን መቁጠር ይቻላል። በምዕራብ ሸዋ በቦታ ስምነት የሚታወቁት እንደ ወሊሶ እና እንደ ማሩ የመሳሰሉት ቦታዎች ጥንት የቀኛዝማች ወርዶፋ ዘር ሀረግ ውስጥ ይገኙ በነበሩት ግለሰቦች የተሰየሙ ሆነው ይገኛሉ። ዘሩን ወደኃላ ስንቆጥር እንዲህ እያለ ይሄዳል። ወርዶፋ፣ጉልማ፣ሉቤ፣ሰንቀሌ፣ፉሌ፣በኬ፣ኖኖ፣ማረቆ፣ማሩ፣ኮዬ፣ወሌ፣ወሊሶ፣ሊበን፣መጫጫ፣ራያ፣ከረዩ፣በዳሶ። የቀኛዝማች ወርዶፋ አባት ጉልማ ሉቤ በቤተሰቡ ሀረግ ከፍተኛ ቦታ ስለነበራቸው አባዱላ ወይም አባወራ የሚባል የጦር ማዕረግ ነበራቸው። ይህም የተሰጣቸው በኦሮሞ የገዳ ሥርአት መሠረት በጦርነት ችሎታቸው ነበር። በተለይም በአንድ ወቅት ከእርሳቸው አካባቢ ውጪ የሚገኙ ከሶዶ፣ ከበቾ፣ ከዲለላ፣ እንዲሁም ከሌላ ቦታዎች ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች አንድ ላይ በመሆን የራሳቸውን አባዱላ በመምረጥና የእሳቸውን አካባቢ በመውረርና ጦርነት በመክፈት በተነሱባቸው ጊዜ ጦሩን በመመከትና በማሸነፍ ድልን በመጎናፀፋቸው ከመቼውም በላይ በአካባቢው ህዝብ በጣም ይፈሩ ጀመር። አፄ ምኒልክ ኢትዮዽያን አንድ ለማድረግ ወስነው ምዕራብ ሸዋን ለማስገበር ጦር በላኩበት ጊዜ የተላከው የራስ ጎበና ጦር ማሩ ከተባለ አካባቢ ሲደርስ የተዋጋው ከወርዶፋ አባት ከጉልማ ጦር ጋር ነበር።

በመጀመርያ የራስ ጎበና የጦር አዛዥ ደጃች ጫጫ የያዙት ጦር እንዶዴ በምትባለው ቦታ ላይ አርፎ ህዝቡን በኃይል ለማስገበር ትልቅ ጦርነት አደረገ። ሆኖም በጉልማ የሚመራው ጦር ሳይበገር ጠንክሮ ስለተዋጋ ተጨማሪ ጦር ከራስ ጎበና መላክ አስፈለገ። አሁንም ደጃች ጫጫ የጉልማን ጦር ማሸነፍ ስላልቻሉ የአካባቢውን ሽማግሌዎች በማግባባት ከጉልማ ጋር ተደራድረውና አስማምተው ህዝቡን እንዲገብር አደረጉ። ደጃች ጫጫ ጉልማን በመጀመሪያ ከራስ ጎበና ጋር አስተዋወቋቸው። ከዚያም ወደ አፄ ምኒልክ አሰቀርበው ልዩ ልዩ ሽልማቶችን እንዲያገኙ ካስደረጓቸው በኃላ የቀኛዝማችነት ማዕረግ ተሰቷቸው ከማሩ ሌላ የጨቦ፣ የአመያ፣ የዱለሌ፣ የወሊሶ እንዲሁም ከጨቦ በስተደቡብ በሚገኙት ቦታዎች ሁሉ ባላባት አድርገው ሾሟቸው። በዚህ አይነት የመንግስትን አስተዳደር ሲመሩ ቆይተው በሞቱ ጊዜ በኦሮሞ ሥርዓት መሠረት ባላባትነትነቱን ከጉልማ የተረከቡት የወርዶፋ ታላቅ ወንድም ደብሱ ነበሩ። እሳቸውም የስመ ጥሩው ጀግና የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ አያት ናቸው።

የአካባቢው ባላባት የሆኑት የደብሱ ጉልማ ታናሽ ወንድም ቀኛዝማች ወርዶፋ ቆራ ተብላ በምትጠራ ከተማ ኑሯቸውን በመመሥረት ወይዘሮ ዘውዲቱ ማንደፍሮን አግብተው የእማዬን እናት ወርቅአበባን ወለዱ። ቆራ በጅማ መንገድ በቱሉቦሎና በወሊሶ መሀል የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት። ሆኖም ጋብቻው ሳይሰምር በመቅረቱና በመለያየታቸው ወርቅአበባ ያለእናት ከአባታቸው ጋር መኖር ጀመረች። እንግዲህ ወርቅአበባ የእናትነትን ፍቅርን ሳታገኝ የአባትዋ እህት ወይዘሮ ተለሉ እንደእናት ክትትል እያደረጉላት በእንክብካቤ ማደግ ጀመረች። ከቤተሰቡ ሥራ ቤት መካከል አንዷ የነበሩትና ጉመሮ ተብለው ለሚጠሩት ልጅ የነበረችው ትርፌ የወርቅአበባ አገልጋይ ሆና ትኖር ነበር። ወርቅአበባና ትርፌ በእድሜ እኩያ ከመሆናቸውም በላይ የማይለያዩና የሚዋደዱም ነበሩ። ወርቅአበባ እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በወቅቱ በነበረው ሥርአት መሠረት ቄስ ተቀጥሮላት አስፈላጊውን ትምህርት በመከታተል ዳዊት ስለደገመች ማንበብና መፃፍ አጠናቀቀች።

ቀኛዝማች ወርዶፋ ከወይዘሮ ተለሉ ሌላ አቶ ተክለማርያም የተባሉ ወንድም ነበሯቸው። አቶ፡ተክለማርያም ቀደም ብለው የሞቱ ሲሆን ባለቤታቸው የነበሩት ወይዘሮ ዘነበች ቆራ የነበራቸውን መሬት ለማየት አዘውትረው ይመጡ ነበር። ወይዘሮ ዘነበች የራስ ብሩ ወልደገብርኤል እህት ስለሆኑ በጣም የተከበሩ ነበሩ። እሳቸውም ወርቅአበባን በጣም ይወዷት ነበር። ደርባባነቷና ትሁትነቷ በጣም ይማርካቸው ስለነበር ወደ አዲስ አበባ ወስደው ለመዳርም ያባብሏት ነበር። ወደ አዲስ አበባም በተመለሱ ጊዜ ስለ ወርቅአበባ ኃይሌ ጎልማሜ ለተባለው መልከ መልካም ወጣት ያጫውቱት ነበር። ኃይሌ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በራስ ብሩ ቤት ያደገ፣ በአዋቂነቱና በቀልጣፋነቱ የተወደደ ከመሆኑም በላይ በራስ ብሩ ቤት ሀብትና ንብረት አድራጊና ፈጣሪ ነበር። ራስ ብሩ ወደ አደባባይ ወይም ከጃንሆይ ችሎት በሚሄዱ ጊዜ መናገር የሚገባቸውን ጽፎ የሚያዘጋጅ አብሮ አደጋቸው ከነበሩት ከአፄ ኃይለሥላሴ ጋር ብዙ ጊዜ እንዳይከራከሩ ወይንም ቅራኔ ዉስጥ እንዳይገቡ መካሪያቸው ነበር። ርስታቸውን በተመለከተ ከነበራቸው መሬቶች መሰብሰብ የሚገባውን ሁሉ በትክክል ተከታትሎና ተቆጣጥሮ የሚሰበስብ ልጅ ኃይሌ ነበር።

ልጅ ኃይሌ ትውልዱ ከሰባት ቤት ጉራጌ ከሙህር ነው። ወላጅ አባቱ አቶ ሶሬ ሲሆኑ እሱ ግን የሚጠራው የወለኔ ወረዳ ገዢ በነበሩትና፣ በክርስትና አባቱ በቀኛዝማች ጎልማሜ ነበር። የልጅ ኃይሌ ቅድም አያት አባ ጥጋቤ በሙህር ከሚገኙት ባላባቶች ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ የሚታወቁ፣ሙህር ውስጥ ደሳ በተባለ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን ዝነኛውን የእየሱስ ገዳም ያቋቋሙ፣ከመቶ ጋሻ መሬት በላይ የነበራቸው ትልቅ ሰው ነበሩ። የልጅ ኃይሌ እናት ወይዘሮ ባይደሴ፣ የአባ ጥጋቤ የልጅ ልጅ የሆኑት አቶ ሶሬን አግብተው ልጅ ኃይሌንና ሌሎች ሦስት ወንዶችና አንድ ሴት ወለዱ። ኃይሌ በጣም ንቁና አእምሮው ለትምህርት የተከፈተ ስለነበረ ገና በሕፃንነቱ በአካባቢው የሚነበብ ነገር ለማንበብ ሕፃኑ ኃይሌ ለሰው እንዲታይ በእንኮኮ አድርገውት የሚነበበውን እንደ እሳት ሲያንበለብል ለሚያየው ሁሉ ያስደንቅ ነበር። ይህንን ሁሌ የሚያዩት ቀኛዝማች ጎልማሜ ገና በልጅነቱ አሥር አመት እንደሆነው ወደ ራስ ብሩ ወልደገብርኤል ወስደው <<ወደፊት ይጠቅሞታል፣ ወስደው ያሳድጉት>> ብለው አስረከቡት። በዚህ ሁኔታ ነበር ወደራስ ብሩ ቤት ገብቶ ለማደግና ለሀላፊነት የበቃው።

ይህ ወጣት ከንቁነቱና ከቀልጣፋነቱ ባሻገር መልክና ቁመናው በጣም ያማረ ዘመናይ ወጣት ስለነበር፣እሱን ለማየትና ለማነጋገር ሁሉም ይጓጓ ነበር። በዚህም የተነሳ በራስ ብሩ ሥር ይኖሩና ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች እንዲህ እያሉ ያሞግሱት ነበር።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የአባ ይስራው ግቢ ጎኑ የተበሳ፣

ኃይልዬን ባየሁት ሲቀመጥ ሲነሳ።

አባ ይስራውማ አባ ይስራው ናቸው፣

እኔ የገደለኝ ጠይሙ አሽከራቸው።

አባ ይስራው ብሩ ጌታዬም አይደሉ፣

ጠይሙ አሽከራቸው ሲገለኝ ዝም አሉ።

 

 

በአንድ ወቅት ወይዘሮ ዘነበች ሁሌ እንደሚያደርጉት ርስታቸውን ለመጎብኘት ወደ ቆራ ብቅ አሉ። በዚያ በመጡበት ጊዜ ቀኛዝማች ወርዶፋ ለአደን ራቅ ወዳለ አገር ሄደው ስለነበር፣ወይዘሮ ዘነበች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ልጃቸውን ወርቅአበባን ለማስኮበለልና ለልጅ ኃይሌ ለመዳር ጥሩ ጊዜ ሆኖ አገኙት። ወርቅአበባም በየጊዜው በሚነገራት የድለላ ቃላቶች የተነሳ ስለተስማማች፣ጊዜ ሳያጠፉ ወርቅአበባን ይዘው አዲስ አበባ ገቡ። የወርቅአበባም አገልጋይ ትርፌ አልለይም ብላ አብራ ሄደች። ወይዘሮ ዘነበች ልጆቹን ይዘው አዲስ አበባ እንደገቡ፣ሁለቱን ልጆች ከሚያከሯቸው በርካታ ቤቶች መካከል በአንዱ ውስጥ እንዲቀመጡ አድርገው ለሠርግ ይዘጋጁ ጀመር። ልጅ ኃይሌም ልጅቷ መምጣቷ ስለተነገረው አስፈላጊውን መሰንዶ ማድረግ ጀመረ።

በ1925 መጨረሻና በ1926 ዓመተ ምህረት መጀመሪያ በአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ የተስቦ በሽታ ገብቶ ሰው ማለቅ ከጀመረ ሰንብቷል። ታዲያ ይህ ተስቦ ማንም ባልጠበቀው ሰዓት እነዚህ ወጣቶች ቤት ገባና ወርቅአበባ በጠና ታመመች። የተስቦ በሽታ የሚጋባ በመሆኑ በሰው ዘንድ በጣም ይፈራ ነበር። ወይዘሮ ዘነበች ወርቅአበባ በተስቦ በሽታ መያዟን እንደተረዱ፣ለራሳቸውና ለሌሎች አገልጋዮቻቸው ጤንነት በማሰብ ከወርቅአበባና ከትርፌ አካባቢ ራሳቸውን አራቁ። ቀድሞውን ከእርሳቸው ይላክ የነበረው የእለት ቀለብ ከመቀነሱም በላይ እስከመቋረጥ ደረሰ። ወጣቶቹ ለከተማው አዲስ ከመሆናቸውም በላይ፣ለወርቅአበባ የህክምና እርዳታን የሚቸራቸው ሌላ የሚያውቁት ሰው ስላልነበራቸው በጣም ችግር ውስጥ ገቡ። በዚህ ጊዜ ትርፌ አካባቢዋን መቃኘት ጀመረች። በአካባቢው ለሚገኙ ሰዎች የቀን ስራ በመስራት በምታገኘው ገንዘብ ማታ ትመጣና ለወርቅአበባ ከምግብ ጀምሮ ሌላም የሚስፈልጋትን ሁሉ በሟሟላት ታስታምማት ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ልጅ ኃይሌ በተለያየ ምክኒያት የሠርጉ ቀን መራዘሙ ከሚነገረው በላይ ስለልጅቷ መታመም ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ወይዘሮ ዘነበችም ከሩቅ ሆነው የልጅቷን ሁኔታ ይከታተሉ ነበር።

ትርፌ የምትችለውን ሁሉ እያደረች ወርቅአበባን በማስታመሟ፣ወርቅበባ ማገገም ጀመረች። የወርቅአበባን ትንሽ ማገገም የተረዱት ወይዘሮ ዘነበች ሠርጉን በአስቸኳይ ለማድረግ ሲጣደፉ ትርፌ ደግሞ በተራዋ በተስቦ ተይዛ ወደቀች። ሆኖም ለወይዘሮ ዘነበች የትርፌ መታመም ምንም ቁምነገር አልነበረውም። ትርፌ በበሽታው ተሸንፋ ስትወድቅ በቅምጥል ያደገችው ወርቅአበባ እሷ ታደርግላት እንደነበረው ሌሎችን አገልግላ ትርፌን ለማስታመም እውቀቱም ሆነ አቅሙ እንደሌላት ስለምታውቅ በሀዘን ተጨብጣ ከማልቀስ ሌላ ምንም ምርጫ አጣች። በዚህ ሁኔታ ላይ ሆና ነበር ሠርጉ ደርሶ ሙሽራው ልጅ ኃይሌ ሙሽራውን ሊረከብ ሠርግ ቤት የመጣው። ወርቅአበባ በሽታ በአደቀቀው ሰውነቷ ላይ ከራስ ብሩ ግቢ በተላከላት የሙሽራ ልብስ አጊጣ፣ዘፈን እየተዘፈነ፣ከበሮ እየተደለቀ ከወይዘሮ ዘነበወርቅ ቤት ሆና ሙሽራው ሲደርስ፣ትርፌ በዚያች የኪራይ ኦና ቤት ትማቅቅ ነበር። ይህም በመሆኑ ወርቅአበባ ያላማቋረጥ እንባ ከአይኗ ይረግፍ ነበር። ልጅ ኃይሌ አምሮና አጊጦ ከሙሽራው ቤት ሲደርስ በቤቱ ይነፍስ ከነበረው የደስታና የዘፈን መንፈስ ይልቅ የሙሽሪቷ የማያቋርጥ ለቅሶ ልቡን ነካው። ለምን እንደምታለቅስም ደጋግሞ ቢጠይቃትም ዝም ብሎ ከማንባት ሌላ ከእሷ ምንም መልስ አላገኘም። በመጨረሻም አንድ ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ በመጠርጠር ልጅቷ ተጠይቃ የምትፈልገው ነገር ካልተሟላ ይዤ አልሄድም ብሎ ወሰነ። በዚህን ጊዜ ወርቅአበባ በነገሩ ግራ ተጋብተውና ከበው ሲጠይቋት ለነበሩት ሰዎች ስለ ትርፌ መታመምና በዚያም የተነሳ እንደሆነ የምታለቅሰው ተናገረች። ይህንንም ለልጅ ኃይሌ ቢነግሩት በነገሩ በጣም አዝኖ ወድያውኑ ሰዎች ልኬ አስወስዳታለሁ ብሎ ተነሳ። ወይዘሮ ዘነበችም "እባክህ ተስቦ ነው የያዛት ሰው ታስጨርሳለህ" ብለው ቢያከላክሉትም ልጅ ኃይሌ ያኔውኑ ትርፌን ወድቃ ከነበረችበት ባዶ ቤት አስወሰዳትና ሠርጉ በሰላምና በደስታ አለፈ። ልጅ ኃይሌ ከሠርጉ በኃላ በሙሽራዋ በበሽታ መጎዳት በጣም አዝኖ፣ሁለቱንም ልጆች ወደ ሆስፒታል ወስዶ በማስተኛት ይዟቸው ከነበረው ሕመም እንዲያገግሙና እንዲሻላቸው አደረገ። ወርቅአበባ ልጅ ኃይሌን ስታገባ እድሜዋ 15ዓመት ሲሆን ልጅ ኃይሌ ደግሞ የ26 ዓመት ጎልማሳና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበር።

ልጅ ኃይሌና ወይዘሮ ወርቅአበባ ኑሯቸውን ራስ ብሩ ሠፈር ለገሀር አካባቢ በማድረግ ትዳራቸውን ጀመሩ። በነሐሴ 13, 1926 እማምዬ ተወለደች። እማምዬ በተወለደችበት ዓመት የኢጣሊያ መንግስት አገራችንን ኢትዮጵያን ለመውረር ከፍተኛ ዝግጅት የሚያደርግበት ጊዜ ነበር። እማምዬ በነሐሴ 1926 ተወልዳ በተከታዩ ዓመት በታህሳስ 1927በወልወል በተደረገው ግጭት ጦርነቱ ተቀሰቀሰ። በጥቅምት 1928 እማዬ እድሜዋ አንድ አመት ከሁለት ወር ሲሆን ፋሽስት ኢጣሊያ የኢትዮዽያን ክልል ጥሳ ወረራዋን ጀመረች። ሁሉም ሰው ለዘመቻ ዝግጅት ጀመረ። በ1928 ጥር ወር የኢትዮዽያ ጦር ከፋሺስት ኢጣልያ የደረሰበትን ጥቃት ለመመከት ወደ ማይጨው በዘመተ ጊዜ ልጅ ኃይሌም በራስ ብሩ አዝማችነት በስራቸው ከሚመራው ጦር ጋር በመሆን ወደ ማይጨው ዘመተ። በዚህ ወቅት እማምዬ አንድ ዓመት ከአምስት ወሯ ሲሆን እናቷ ወይዘሮ ወርቅአበባ ደግሞ ሁለተኛ ልጇን ነፍሰጡር ነበረች። በማይጨው ዘመቻ ወርቅአበባ ባለቤቷ ብቻ ሳይሆን አባቷም ቀኛዝማች ወርዶፋ ዘምተው ስለነበር አዲስአበባ መቆየት ነበረባት። የወርቅአበባ አገልጋይ የነበረችው ትርፌም እነዚህን ጀግኖች ተከትላ ወደ ጦርነቱ ዘመተች።

የፋሽስት ጦር ማይጨው ላይ ድል አግኝቶ የኢትዮዽያ ጦር ተፈታ። ልጅ ኃይሌ ከማይጨው ሲመለስ ወንድ ልጅ ተወልዶ ጠበቀው። ስሙንም አበራ ብሎ ጠራው። ከዚያም ራስ ብሩ ከጃንሆይ ጋር ስደት ስለሄዱና ከተማውም ስለተሸበረ፣ልጅ ኃይሌ ባለቤቱን ወርቅአበባንና ልጆቹን ይዞ ወደ ትውልድ አገሩ ወደ ምሁር መሄድ ፈለገ። ሆኖም የሚያስፈልገውን መሰንዶ ለማድረግ በቅድሚያ ብቻውን መሄድ ስለፈለገ ለጊዜዉ ባለቤቱንና ልጆቹን ወደ ወርቅአበባ አባት ቀኛዝማች ወርዶፋ መኖሪያ ወደ ቆራ ከተማ ወሰደ።

ወርቅአበባ ተወልዳ ካደገችበት ከተማ ቆራ እንደደረሰች አባቷ ቀኛዝማች ወርዶፋ ከማይጨው ተመልሰው በዚያ አገኘቻቸው። በጦርነቱም ላይ ቆስለው ነበር። ልጅ ኃይሌ ወደ ትውልድ አገሩ ወደ ሙህር ገብቶ አስፈላጊውን መሰንዶ ጨርሶ ባለቤቱንና ልጆቹን ለማምጣት መንገድ ሲጀምር በወቅቱ በጉራጌና በአድያ ብሀረሰቦች መሀል ግጭት ስለተፈጠረ መንገድ በመዘጋቱ የተነሳ ማለፍ አቃተው። በዚህም የተነሳ ለአጭር ጊዜ ብሎ ባለቤቱንና ልጆቹን ትቶ የሄደው ልጅ ኃይሌ ሳይመለስ ብዙ ቆየ። ወቅቱ የግርግር ጊዜ ስለነበር ስለተፈጠረው ሁኔታ የሚገልፅ መልእክት እንኳን ለመላክ ዕድል ባለመገኘቱ፣ የልጅ ኃይሌ በቶሎ አለመመለስ ወርቅአበባንና አባቷን ብዙ ሀሳብ ውስጥ ከተተ።

በዚህ ጊዜ ጣልያን ቀኛዝማች ወርዶፋ በነበሩበት ከተማ መግባት ብቻ ሳይሆን ወደ ጣልያን እንዲገቡ ሊያባብላቸው ይሞክር ነበር። እሳቸው ግን ወንድሞቻቸው ከሆኑት ከእነ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጋር ጫካ ገብቶ ለመዋጋት ይዘጋጁ ነበር። ሆኖም ወርቅአበባንና ልጆቿን ለጣሊያን ትቶ ጫካ መግባት ሊያስከትለዉ የሚችለዉን መዘዝ በመፍራት በነገሩ ያስቡበትና የከተማውን ሽማግሌዎች ያማክሩበት ጀመር።ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ብዙ ጊዜ አባብሎ ያቃተው ጣሊያን በንዴት ይተናጎላቸው ጀመር።በመሬታቸው ላይ ቀን የሚያስተክሉትን ዛፎች እና ችግኞች የራሱን ሰዎች እየላከ ያስፈርስባቸዋል።

ቀኛዝማች ወርዶፋ በቂ ጊዜ ከታገሱ በኃላ ልጃቸውን ወርቅአበባን ለሌላ ሰው በመዳር ልጃቸውን እና ልጆቿን በማትረፍ እሳቸው በአርበኝነት ለመዋጋት ቆረጡ። እዚያውም ወርቅአበባ ልጅ ኃይሌን ከማግባቷ በፊት ለጋብቻ ጠይቀው የነበሩት አቶ ንጋቱ ደስታ በዚያው አካባቢ ስለተገኙ ስለጉዳዩ ተጠየቁ። እሳቸውም ያለምንም ማንገራገር ስለተስማሙ ሰርግ ይደገሳል። ለሠርጉ ዋዜማ ዳስ ተጥሎ እየተጨፈረ እየተዘፈነ እያለ የልጅ ኃይሌ ሁለት ወንድሞች ከሌሎች አራት አሽከሮች ጋር ስድስት በቅሎዎች ይዘው ተልከው ወርቅአበባን እማምዬንና አበራን ለመውሰድ መጡ።የደረሱት ለሠርጉ ዋዜማ ስለነበር ሠርጉን ተመልክቶ ባዶ እጃቸውን ከመሄድ በቀር ሌላ ምንም ምርጫ አልነበራቸውም።

ከሠርጉ በኃላ ቀኛዝማች ወርዶፋ ለወርቅአበባ አዲስ ባለቤት ለአቶ ንጋቱ እርጥብ ሣር ነጭተው በምድር የሰጠሁህን በሰማይ እቀበልሀለው ብለዋቸው እርሳቸው ከሌሎች ወንድሞቻቸዉ ከሆኑት ከነደጃዝማች ገረሱ ጋር በአርበኝነት ለመዋጋት ጫካ ገቡ። ከዚያ በኃላ እማምዬ አበራና እናታቸው ወርቅአበባ ከአቶ ንጋቱ ጋር መኖር ጀመሩ። አቶ ንጋቱ በጣም ትሁትና ደግ አባት ነበሩ። እማዬንና አበራን በጣም ይወዱ ነበር። ወደ አዲስ አበባ በሄዱ ቁጥር ልብስ ይዘውላቸው ይመጡ ነበር። ወርቅአበባንም በጣም አክብረው ይዘዋት ነበር። እንግዲህ እማምዬና አበራ ነፍስ ሲያውቁ የሚያስታውሱት አባታችው አቶ ንጋቱን ነበር።

እማምዬ ነፍስ ማወቅ እንደጀመረች አንድ የምታስታውሰው ነገር ነበር። ይሀውም አንድ ቀን እናቷ ቀኑን ሙሉ ምግብ ስታዘጋጅና ስታሰናዳ ውላ በምሽቱ የአቶ ንጋቱ ወንድም ወደ ሆኑት ባሻ መኩሪያ ቤት እማዬንና አበራን ይዛ ሄዳ አንድ ጠና ያሉ መልከመልካም ረዥም ቀይ ሰው፣ ፊታቸው በፈገግታና በደስታ የተሞላ ከእንግዳ መቀበያው ክፍል ተነጥፎላቸው ምሽቱን ሁሉ ሲስተናገዱ እንዲሁም እሷንና አበራን እያቀፉ ሲስሙና ሲያጫውቷቸው እንዳመሹ ትዝ ይላታል። አያቷ ቀኛዝማች ወርዶፋ ነበሩ። ጠላትን በአርበኝነት ለመውጋት ጫካ ከገቡ ከዓመት በላይ ሆኗቸው ነበርና ቀኑ ከጨለመ በኃላ ልጃቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ለማየት ከጠላት ተደብቀው መምጣታቸው ነበር። እማምዬ ለመጀመርያ እና ለመጨረሻ ጊዜ አያቷን ያየችው የዚያን እለት ነበር። ቀኛዝማች ወርዶፋ ከስመ ጥሩው ጀግናና ከወንድማቸው ልጅ ከሆኑት ከደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጋር በአርበኝነት በመሰለፍ ጠላትን መድረሻ አሳጥተው ነበር። የነደጃዝማች ገረሱ ጦር በተፈለገ ጊዜ ብቻ የሚሰባሰብ ጦር ነበር። ጥቃትን ለማድረግ ሲያስፈልግ በተጠራ ጊዜ አንዳንዴ እስከ 40,000 እና 50,000ጦር ሲሰባሰብ ከውጊያው በኃላ ደጃዝማች ገረሱ ጥቂት እራሳቸውን ብቻ ሆነው ይቀራሉ። በዚህ ሁኔታ የጠላትን ጦር ሲያርበደብዱ በጣሊያን ጦር ያልወጣባቸው አዋጅና ያልተወሰነባቸው ውሳኔ አልነበረም። በዚህ መሀል ከመካከላቸው የሚሞቱና የሚሰው ብዙ ጀግኖች ነበሩ። ህዳር 5 ቀን 1930ዓመተ ምህረት የገረሱ ጦር ጭቱ አጠገብ ጣጤሳ በሚባል ቦታ እንደሰፈረ ለፋሺስት ኢጣሊያ ገብቶ የራሱን አገር በሚወጋው በራስ ኃይሉ ጦር ተከበበ። የጠላትም ጦር በታንክ በመትረየስ የተደራጀ ከመሆኑም በላይ የአውሮፕላንም ድጋፍ ስለነበረው የገረሱን ጦር ከፍተኛ ጉዳት አደረሰበት። ብዙዎች ወታደሮች ቆሰሉ ብዙዎችም ሞቱ። ጦርነቱ እያየለ ስለመጣም የገረሱ ጦር ማፈግፈግ ነበርበት። ሁሉም ወደኃላ ሲያፈገፍጉ ቀኛዝማች ወርዶፋ መትረየሳቸውን እየተኮሱ ከተቀመጡበት አልነሳም አሉ። እነ ገረሱም ቢለምኗቸውም አልሄድም ብለው ብቻቸውን ወደእርሳቸው በሚመጣው የጠላት ጦር ላይ መትረየሳቸውን ያዘንቡበት ነበር። በዚህ ሁኔታ ሁሉም ነፍሱን ለማዳን ሸሽቶ ሲያመልጥ፣ቀኛዝማች ወርዶፋ ጉልማ እና ግራዝማች ሰብስቤ ዘለለው በዚሁ ጦርነት ላይ አረፉ።

© 2023 by  Memorial. Proudly created with Wix.com

bottom of page