top of page

                   ይህ ከዚህ ቀጥሎ የሚነበበው ከልጆቻቸው አንዱ ያስተላለፈው መልዕክት ነው።

 

 

እኤአ በ 1988  ዓ ም፣ በአዲስ አበባ ከተማ፣በዕለተ ሰንበት፣በልደታ ቤተክርስትያን ቅጥር ግቢ ውስጥ አንድ የሁለት ሳምንት ዕድሜ የሚሆነው ሕፃን ብቻውን ሆኖ እያለቀሰ ተገኘ። ቀኑ እሁድ ስለነበር በርካታ ሰው በቤተክርስትያኑ ይገኝ ነበር። በቤተክርስትያኑ የሚደረገው ሥርዓት ተፈፅሞ ሰው ሁሉ ወደየቤቱ መሄድ ሲጀምር፣ በሕፃኑ ብቸኝነትና መሪር ለቅሶ በማዘን ብዙ ሰው መሰብሰብ ጀመረ። ዘውትር ከቤተክርስትያን የማይቀሩት ወይዘሮ አልማዝም ሥርዓተ ቅዳሴ ከተከታተሉ በኃላ ወደቤታቸው ለመሄድ ሲነሱ በቤተክርስትያኑ ግቢ ሰው ተሰብስቦ በማየታቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ ከተሰበሰበው ሰው መሐል ብቅ አሉ። ወይዘሮ አልማዝም በሕፃኑ ያለ ወላጅ መቅረት በጣም ስላዘኑ እዚያ የተሰበስቡትን ሰዎች ጥያቄ ይጠይቁ ነበር። ብዙዎቹ ሕፃኑን ብቻውን እያለቀሰ እንዳገኙት ሲናገሩ፣ አንዳንዶቹ ግን አንዲት ወጣት ሕፃኑን ይዛ ተቀምጣ እንደነበረና ከዚያም ሳይታሰብ አስቀምጣው እንደሄደች ይናገሩ ነበር። ወይዘሮ አልማዝ ለሕፃኑ በጣም በማዘን ምናልባት ወላጅ እናቱ ተመልሳ ትመጣ እንደሆን ተስፋ በማድረግ ከተሰበሰበው ሰው ጋር እዚያው መጠበቅ ቀጠሉ። ሆኖም ማንም ልጄ ነው ብሎ የመጣ ሰው አልነበረም።

 

              እዚያም አብረው ከቆሙት ሰዎች መካከል ገፍቶ ለሕፃኑ እርዳታ ለማድረግ የፈለገ ሰው ባለመኖሩ ወይዘሮ አልማዝ ተከትላቸው የነበረችውን ባለሟል እንድትሸከመው አድርገው ወደ መኪናቸው ለመሄድ ሲነሱ እዚያ ከነበሩት ሰዎች የምስጋና ቃል መጉረፍ ጀመረ። ሕፃኑ ገና የሁለት ሳምንት ዕድሜ የነበረው ሲሆን በጣም ተጎድቶም ነበር። ከዚያም በተከታዩ ሁለት ሳምንታት የወላጅ እናቱ መጥታ ብትረከበው፣ ወይዘሮ አልማዝ እንደሚረዷት በድምፅ ማጉያ ቢነገርም ማንም ሳይመጣ ቀረ። ወይዘሮ አልማዝ በወቅቱ ልጆቻቸውን ሁሉ አሳድገውና አስተምረው አንዳንዶቹንም ለወግ ማዕረግ አብቅተው ስለነበር ሕፃኑ በቤቱ ውስጥ እንደ ብርቅ ሆነ። በዚያን ጊዜ ከትንሿ ሴት ልጃቸው በስተቀር ሁሉም ልጆቻቸው በአሜሪካንና ካናዳ ይኖሩ ነበር። ሕፃኑን አሳክመው በእንክብካቤ ማሳደግ ሲጀምሩ በውጪ የሚገኙት ልጆቻቸው እናታቸውንና ትንሿ እህታቸውን ለማስወሰድ ጀምረውት የነበረው ጉዳይ አለቀ። በዚህ ጊዜ ይህንን ሕፃን ትቶ መሄድ ለወይዘሮ አልማዝ በጣም ትልቅ ችግር ነበር። ልጆቻቸው ጋር መሄድ ግድ ስለነበር ሕፃኑን ለቅርብ ዘመድ በአደራ ትቶ መሄድ አስፈላጊ ሆነ። 

 

          ወይዘሮ አልማዝ ኢትዮጵያን ለቀው ወደውጪ ለመኖር በወጡበት ጊዜ ሕፃኑ የሰባት ወር ልጅ ነበር። ወይዘሮ አልማዝ ካናዳና አሜሪካ እንደመጡ ይህንን ልጅ ወደ ውጪ ለመምጣትና ለመኖር ዕድሉ እንዲደርሰው አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ለራሳቸው ቃል ገቡ። ወዲያውም በአሜሪካን የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት ዕድሉ ሲገጥማቸው፣ይህንን ሕፃን ከልጆቻቸው ሳይለዩ በማስመዝገባቸው ልጁ የአሜሪካ የመኖርያ ፍቃድን ለማግኘት ቻለ። ይህ ልጅ በአዲስ አበባ በተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች እየተማረ፣የሚስፈልገው ነገር ሁሉ ከአሜሪካንና ከካናዳ እየተላከለት በብዙ አገልጋዮች እየተጠበቀ በእንክብካቤ ካደገ በኃላ ወደ አሜሪካንና ካናዳ በመምጣት ከሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ተቀላቀለ። በአሜሪካን ኑሮውን በጀመረበት ወቅት የወላጅ እናቱ ማን እንደሆነች ማወቅ በጣም ይፈልግ እንደነበር የሚያውቁት ወይዘሮ አልማዝ ለልጁ የመንፈስ እረፍትን እንዲያገኝ በማሰብ ወደ ኢትዮዽያ በመሄድ ከሀያ ዓመት በፊት ትታው የሄደችው የዚህ ልጅ እናት ማን እንደሆነች ለማወቅ ትግሉን እንደ አዲስ ተያያዙት። ከብዙ ውጣ ውረድ በኃላ ያቺ በሁለት ሳምንቱ ትታው የሄደችው ወላጅ እናቱ ልትገኝ ቻለች። ወይዘሮ አልማዝም ይህችን በጣም ዝቅተኛ ኑሮ የምትኖር ሴት ትልቅ መሥሪያ ቤት በማስቀጠርና አስፈላጊውን ሁሉ እርዳታ በማድረግ ኑሮዋ እንዲሻሻል አድርገዋል። በአመቱም ልጁ ኢትዮጵያ ሄዶ የማያውቃትን ወላጅ እናቱን እንዲተዋወቅ ተደረገ።

 

             ይህም ልጅ በአሁኑ ሰዓት በድንግል ማርያም ቤተክርስትያን መዘምራን ሆኜ የማገለግለው እኔ ኤልያስ ሻውል ነኝ። እማምዬ፣ ከሰው በላይ የምወድሽና የማከብርሽ፣ከራስሽ አስቀድመሽ ለሰው የምትደርሺ ትልቅ ሰው ነሽ። ለተቸገሩ ሰዎች ፈጥኖ ደራሽ ለመሆንሽ የእኔ ታሪክ በቂ ምስክር ነው። ገና የሁለት ሳምንት ልጅ ሆኜ፣የሚደርስልኝ ጠፍቶ ሕይወቴን አዳንሽው። ማንም ሊያደርገው ከሚገባው በላይ በእንክብካቤ እንዳድግ አደረግሽ። ከአገኘሽኝ ጊዜ ጀምሮ ያለሽን ሁሉ ከፍቅር ጋር ለእኔ በመለገስ እዚህ እንድደርስ አድርገሻል። የምጓዘው መንገድ እና የምከተለው ዓላማ ክርስትያናዊ እንዲሆን ያስተማርሺኝ አንቺ ነሽ። አንቺ ባትደርሽልኝ ኖሮ ሕይወቴ ምን ሊሆን እንደሚችል ሳስብ፣ አንቺንና እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ። ሕይወቴን አትርፈሽ የምወዳቸውና የሚወዱኝ እና እንደ ራሳቸው ልጆች የሚያዩኝ ወንድሞችና እህቶች ሰጠሽኝ። የእኔ አሁን በሕይወት መኖር ዋና ምክኒያቱ አንቺና እግዚአብሄር ናችሁ። እማምዬ ያደረግሽልኝን ሁሉ እስከ ሕይወቴ መጨረሻ ድረስ አልረሳሁም። አንቺ የአደረግሽልኝን ውለታ ለመክፈል እጅግ በጣም ከባድ ስለሆነ እግዚአብሄር ይክፈልሽ እላለሁ። አምላኬንም አንቺን እናት አድርጎ ስለሰጠኝ አመሰግነዋለው።

 

 

     በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፣እኔ አውቃቸዋለሁ፣እነርሱም ይከተሉኛል፣እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፣ከቶ አይጠፉም፣ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም። እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፣ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም። የዮሐንስ ወንጌል ም10 ቁ 27 -29

 

ወጣት ኤልያስ ሻዉል

.

bottom of page