top of page
"emamye yehulum enat"

 

 

Almaz Haile

Born August 18th, 1934

 Mother, grandmother, great-grandmother and loving.

 Sadly left us on May 16, 2015

 

Do not stand at my grave and weep
I am not there. I do not sleep.
I am a thousand winds that blow.
I am the diamond glints on snow.
I am the sunlight on ripened grain.
I am the gentle autumn rain.
When you awaken in the morning's hush
I am the swift uplifting rush
Of quiet birds in circled flight.
I am the soft stars that shine at night.
Do not stand at my grave and cry;
I am not there. I did not die.  

                                      MEF                      

 

መልካሙን ገደል ተጋድዬአለሁ

ሩጯውን ጨርሼአለሁ

ሃይማኖቴን ጠብኬአለሁ

2ኛ ጢሞቴዎስ 4 : 7

 

ወይዘሮ አልማዝ ኃይሌ

 አጸደ ማርያም

ነሐሴ 12 1926

        ግንቦት 7 2007

 

 

 

 

 

 

ወይዘሮ አልማዝ ኃይሌ ከአባታቸው ከበጅሮንድ ኃይሌ ጎልማሜና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወርቅአበባ ወርዶፋ እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር  ነሐሴ 12ቀን 1926 ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ ከተማ ለገሀር አካባቢ ተወለዱ። በተወለዱ በአንድ አመታቸው ጠላት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በመዉረሩ ወይዘሮ አልማዝ ከነቤተሰባቸው መንከራተት አጋጥሟቸው ነበር። ጠላት ተደምስሶ አገራችን ነፃነቷን ከአገኘች በኃላ የእናታቸው አጎት ልጅ የነበሩት ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ አገር እንዲያቀኑ ወደ ወላሞ ከዚያም ወደ ጎሙጎፋ በሄዱ ጊዜ ብዙ ዘመዶቻቸው ተከትለዋቸው ነበርና ወይዘሮ አልማዝ እናታቸውን ተከትለው ሄደው ነበር። በዚያ ወቅት እድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ ስለነበር በወቅቱ ዘመናዊ ትምህርትን ለመከታተል በመጀመርያ በወላሞ ከዚያም በዘመኑ ጭንቻ በአሁኑ ጊዜ አርባ ምንጭ ተብሎ በሚጠራው ከተማ ይገኙ በነበሩ ትምህርት ቤቶች በመግባት አስፈላጊውን የቀለም ትምህርት ተከታትለዋል። ከዚያም አዲስ አበባ ይገኝ ወደነበረው ቀበና ሚስዮን በመግባት ትምህርታቸውን ቀጥለዋል።

ወይዘሮ አልማዝ ኃይሌ በ1945 ዓመተ ምህረት ከልጅ ሻውል ገብረመስቀል ጋር ጋብቻ በመመስረት ስምንት ልጆችን አፍርተዋል። ወይዘሮ አልማዝ የትዳር አለም ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ደከመኝ ታከተኝ ሳይሉ ልጆቻቸውን ከመንከባከብ ባሻገር ሌሎች የሚያሳድጓቸውና የሚያስተምሯቸው ብዙ ነበሩ። እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር በ1963ዓ ም የሚወዷቸው የትዳር ጓደኛቸውና የልጆቻቸው አባት የሆኑት ልጅ ሻውል ገብረመስቀል በ46ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ወይዘሮ አልማዝ እድሜያቸው 36 ዓመት ብቻ ነበር። ከባለቤታቸው እረፍት በኃላ ልጆቻቸውን በእንክብካቤ ማሳደግና የነበራቸውን ሰፊ ቤተሰብ ማስተዳደር ቀላል እንዳልነበረ ሁሌ ይናገሩት ነበር።

ይህንንም ግዴታ ለመወጣት ሌላ የትዳር ጓደኛ ሳይሹ ልጆቻቸውን ሁሉ አሳድገውና አስተምረው ለወግ ለመዐረግ አብቅተዋል። በተለይም በኢትዮዽያ የመንግስት ለውጥ ተደርጎ የደርግ መንግስት በተተካ ጊዜ፣ ለወይዘሮ አልማዝ ብቸኛ መተዳደሪያ የነበሩት የግል ንብረቶች ሁሉ በመወረሳቸው ከፍ ያለ ችግር ውስጥ ቢገቡም፣የልጆቻቸው እንክብካቤ እንዳይጓደል በማሰብ ወደ ንግድ አለም በመግባት የመጣውን ችግር ተወጥተውታል። የደርግ መንግስት በወጣቶች ላይ ጥቃትን በመሰንዘር ልጆች በጨረሰበት ወቅት፣ወይዘሮ አልማዝ ልጆቻቸውን ለማትረፍ ይህ ነው የማይባል ጥረት በማድረግ በወቅቱ በኢትዮዽያ የነበሩትን ልጆቻቸውን ወደ አሜሪካን በመላክ ከትልቅ አደጋ እንዲድኑ አድርገዋል። ከዚህ በኃላ ወይዘሮ አልማዝ በጣም ከሚወዷቸውና ከሚያፈቅሯቸው ልጆቻቸው ጋር በውጪ አገር ለመኖር እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር በ1980 ዓ ም ከአገራቸው ወጡ።

ወይዘሮ አልማዝ ከኢትዮጵያ ሲወጡ በመጀመርያ ወደ ቶሮንቶ ካናዳ ከዚያም ወደ ሎሳንጅለስ ካሊፎርኒያ ከልጆቻቸው ጋር ደስታና ተድላ የተጎናፀፈውን ኑሮ ተጉዘዋል። በነዚህ ከተማዎች በተቀመጡበት ጊዜያት ለክርስትና ሀይማኖት በነበራቸው ፅኑ እምነት በመነሳት በቶሮንቶ ለሚገኘው ቅድስት ማርያም የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን እና በሎሳንጅለስ ለሚገኘው የድንግል ማርያም የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሳትን ከኢትዮዽያ በማስመጣት፣ አያሌ በሆኑ የቤተክርስትያን መሀበሮች በመሳተፍና ካህናቶቹን በሚያስፈልገዉ ሁሉ በመርዳት እጅግ ከፍ ያለ አስተዋፆዎ አበርክተዋል። በተለይም ሁልጊዜ ለምእመናኑ ያሳዩት በነበረው ፍቅር የተሞላበት ፈገግታና ቸርነት የተነሳ በቤተክርስትያን የሚያውቋቸው በርካታ ምዕመናን ሁሉ "እናታችን" በሚል ተቀጽያ ይጠሯቸው ነበር። ወይዘሮ አልማዝ ኃይሌ የመጀመሪያ ልጃቸው ገባይነሽ ሻውል በ1984 ዓ ም ከዚህ አለም በሞት በመለየቷ ከፍ ያለ ሀዘን ውስጥ ወድቀው ነበር።

ወይዘሮ አልማዝ በእግዚአብሄር ፀጋና በረከት የ16 ልጆች አያት፣ የሁለት ሕፃናቶች ደግሞ የቅድም አያት ለመሆን የበቁ ታላቅ እናት ነበሩ። ወይዘሮ አልማዝ በዚች ትተዋት ከሄዱበት ዓለም በኖሩበት ዘመን በቅርብም ሆነ በሩቅ ለሚያውቋቸው ሰዎች፣ ማንንም ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ሁሌ በሚያሳዮት ፍቅርና አክብሮት የተነሳ ከእርሳቸው በእድሜ ለሚያንሱ ሁሉ እውነተኛ እናት፣ አብረዋቸው ለነበሩት ጓደኞቻቸው ተወዳጅ እህት በመሆን፣ በቤተክርስትያንም ሆነ በጠቅላላው ህብረተሰብ መወደድን ያተረፉ ትልቅ ሰው ነበሩ። ወይዘሮ አልማዝ በችግርና በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት በነበራቸው ጉጉት የተነሳ በአገራችን የሚረዷቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ፣አሁንም አሉ። በወይዘሮ አልማዝ ኃይሌ በየወሩ የገንዘብ ተቆራጭ እየተደረገለት ቤተሰቡን የሚያስተዳድር ብዙ ከመሆኑ ባሻገር፣በየጊዜው ገንዘባቸውን የሚለግሷቸው የእርዳታ ድርጅቶችም ይገኙበታል። ሰው ሲሻሻል ያስደስታቸው ስለነበር ብዙዎችን ገንዘብ በመለገስና በመምከር ንግድ ውስጥ ገብተው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ አድርገዋል።

ወይዘሮ አልማዝ በሆስፒታል ተኝተው በነበረበት ጊዜ፣ ለልጆቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው ከተናገሩት መልዕክት መካከል ለመጥቀስ ያህል ከብዙ በጥቂቱ ከዚህ ቀጥሎ አስፍረነዋል። "….....ለእኔ የወለድኳቸው ልጆቼ ብቻ ሳይሆኑ ያገቧቸውም ሁሉ የዋሉልኝ ውለታ እጅግ ብዙ ነው። እኔ ጎደለብኝ የምለው አንዳችም ነገር የለም። እናንተ ለአደረጋችሁልኝ ውለታ ከምስጋና እና ከምርቃት በስተቀር ሌላ የምከፍላችው ከቶ አይቻለኝም። ለእኔ ገንዘቤ እናንተ ናችሁ። እግዚአብሄር ላደረጋችሁልኝ ሁሉ ውለታ ብድሩን እሱ ይመልስላችው። በእውነቱ በልጆቻችሁ እንኳን ታገኙታላችሁ ብዬ ተስፋ አላደርግም። ምክኒያቱም የዛሬ ልጆች እንደናንተ አይሆኑም። እንደናንተ የሚሆን ልጅ አይወለድም። ከተወለደም እግዚአብሄር የባረከው፣ እግዚአብሄር የቀደሰው መሆን አለበት። እግዚአብሄር ልጆቻችሁን ይባርክላችሁ ፣ ለቁም ነገርም ያብቃላችሁ ። የአደረጋችሁልኝን ሁሉ በልጆቻችሁ ይመልስላችሁ። እግዚአብሄር ከፃድቃን እኩል አቁሞ ከምድረ ሰማያት ሰማያዊ መንግስትን፣ አዲስቷን እየሩሳሌምን ያውርሳችሁ ። ሌላ አንድ የምጨምረው ነገር አለ ለእኔ ቀኔን የሚያውቀው እግዚአብሄር ብቻ ነው። መቼ እንደቆረጠልኝም ቀኑን አላውቅም። አሁን እንደማየሁ ሁነታዬ ጥሩ አይደለም። እኔ ሰው ሁሉ እንደሚሞተው እሞታለሁኝ። ሞትም ለእኔ ቁምነገር አይደለም። በሞትኩኝ ጊዜ ጥቁር ለብሳችሁ፣ከሰል መስላችሁ፣ አፈር መስላችሁ እንዳትታዩ። ዋጋ የለውም። ነጭ ልብስ ለብሳችሁ፣ ሻማ አብርታችሁ፣ ከበሮ እያስመታችሁ፣ ሥርዐተ ቅዳሴውን አስፈፅማችሁ ሸኙኝ። ከቀብሬ በኃላ ለቅሶና ሀዘን እንዳይኖር። ከዚህ በላይ የተናገርኩትን እንድታደርጉ በመሀይም ቃሌ ገዝቻችኃለው። ይህንን ስነግራችሁ አባታችን አባ ላይከማርያም በዚህ ይገኛሉና ምስክሬ እሳቸው ናቸው።''...

     ወይዘሮ አልማዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደረሰባቸው ሕመም የተነሳ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ነበር። ሆኖም ፈጣሪ እግዚአብሄር የራሱ ምክኒያት ስላለው ወደ እርሱ ሊወስዳቸው በፈቀደ ጊዜና በእልፈታቸው ሰዓት እንደ ኢትዮጵጵያ አቆጣጠር አርብ ግንቦት 7 2007 በልጆቻቸው እንዲሁም በልጅ ልጆቻቸው ተከበው በዝማሬና በፀሎት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

 

 

በዚህ በኃዘናችን ጊዜ ከጎናችን በመሆን ደከመን ሰለቸን ሳትሉ በአጠገባችን በመሆን ላልስተዛዘናችሁን ሁሉ እግዚአብሄር የድካማችሁን ይክፈላችሁ እንላለን። እንዲሁም እናታችን በተፈጥሮዋ ሰው ለማስተናገድ ተጨናቂ መሆኗን ስለምናውቅ፣ በሕመም ላይ ሆና እንዳትጨነቅ በማሰብ ፣ የቤቱን ርቀት ጥያቄ ውስጥ ሳታስገቡ መጥታችው ለመጠየቅ ፈልጋችሁ ላልተሳካላችሁ ሁሉ ከልባችን ይቅርታ እንጠይቃለን። በዚህ አጋጣሚ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ በስልክ ላነጋገራችሁንና መልእክት በመተው ላፅናናችሁን ሁሉ እግዚአብሄር ያክብርልን እንናለን።

 

bottom of page